1 ነገሥት 3:4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ገባዖን ፈጽማ ትሰፋ ነበርና በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ ዘንድ ተነሥቶ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ በገባዖን አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዋ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከሁሉ የሚበልጠው የማምለኪያ ኰረብታ ገባዖን ስለ ነበረ፣ ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰሎሞን በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺሕ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ታላቁ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለ ነበር አንድ ቀን ሰሎሞን መሥዋዕትን ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ፤ ከዚህም በፊት በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ታላቅ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለ ነበር አንድ ቀን ሰሎሞን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ፤ ከዚህም በፊት በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦአል፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። |
ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስለ ሰላም መሥዋዕት ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችንና መቶ ሃያ ሺህ በጎችን አቀረበ። ንጉሡና የእስራኤል ልጆች ሁሉ እንዲሁ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ፤ አከበሩም።
ካህኑን ሳዶቅንና ካህናቱን ወንድሞቹን በገባዖን በኮረብታው መስገጃ ባለው በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት አቆማቸው፥
ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ።
ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ሁሉ ተናገረ።
ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር የምስክር ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታው መስገጃ ሄዱ።
ንጉሡ ሕዝቅያስም ስለ ቍርባን ሺህ ወይፈኖችንና ሰባት ሺህ በጎችን ለይሁዳና ለጉባኤው ሰጥቶ ነበር፤ አለቆቹም ሺህ ወይፈኖችንና ዐሥር ሺህ በጎችን ለጉባኤው ሰጥተው ነበር፤ ከካህናቱ እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና።
በዚያችም ዕለት ንጉሡ ሰሎሞን ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችንና መቶ ሃያ ሺህ በጎችን ሠዋ። እንዲሁ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ አከበሩ።
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ በዚያ ዓመት፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ፥ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ሐሰተኛው ነቢይ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦
ገባዖን ከመንግሥታት ከተሞች እንደ አንዲቱ ታላቅ ከተማ ስለሆነች፥ ከጋይም ስለ በለጠች፥ ሰዎችዋም ሁሉ ኀያላን ስለ ነበሩ እጅግ ፈራ።