1 ሳሙኤል 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በፍልስጥኤማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት 1 ሳኦልም በእስራኤል ላይ ከነገሠ ሁለት ዓመት ሆነው፥ 2 ያንጊዜም ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎችን ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማኪማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፤ አንዱም ሺህ በብንያም ገባዖን ከልጁ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱን ወደ ድንኳኑ አሰናበተ። 3 ዮናታንም በኮረብታው የነበሩትን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም፦ እስራኤል ይስሙ ብሎ በሀገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ። 4 እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ በረቱ ሰሙ፤ ሕዝቡም ደንፍተው ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልጌላ ተሰበሰቡ። 5 ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች፥ ስድስት ሺህም ፈረሰኞች፥ በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤቶሮን በአዜብ በኩል በማኪማስ ሰፈሩ። 6 የእስራኤልም ሰዎች ወደ እነርሱ መሄድ እንደሚያስጨንቃቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በግንብ፥ በገደልና በቋጥኝ፥ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ። 7 ዮርዳኖስንም ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር የሄዱ አሉ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልጌላ ነበረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው እርሱን መከተልን ትተው ተበተኑ። ሳሙኤል ሳኦልን እንደ ገሠጸው 8 ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቈየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልጌላ አልመጣም፤ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ። 9 ሳኦልም፥ “የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ” አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ። 10 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲባርከው ሊገናኘው ወጣ። 11 ሳሙኤልም፥ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” አለ። ሳኦልም፥ “ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በነገርኸኝ መሠረት በቀጠሮው ቀን እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማኪማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤ 12 ስለዚህ፦ ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ እኔ ወደ ጌልጌላ ይወርዱብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ፊት አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ደፍሬ የሚቃጠል መሥዋዕትን አሳረግሁ” አለ። 13 ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “በድለኻል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዙን አልጠበቅህምና፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጽንቶልህ ነበር። 14 ከእንግዲህ ወዲያ ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ንጉሥን ያነግሣል” አለው። 15 ሳሙኤልም ከጌልጌላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከትለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልጌላም ተነሥተው ወደ ብንያም ገባዖን መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፤ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። 16 ሳኦልና ልጁ ዮናታንም፥ ከእነርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ በብንያም ገባዖን ተቀምጠው አለቀሱ፤ ፍልስጥኤማውያንም በማኪማስ ሰፈሩ። 17 ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር ማራኪዎች በሦስት ክፍል ሆነው ወጡ፤ አንዱም ክፍል በጎፌር መንገድ ወደ ሦጋክ ምድር ሄደ። 18 ሁለተኛው ክፍል ወደ ቤቶሮን መንገድ ዞረ፤ ሦስተኛውም ክፍል በገባዖን መንገድ ባለው ወደ ሴቤሮም ሸለቆ በሚመለከተው በዳርቻው መንገድ ዞረ። 19 ፍልስጥኤማውያንም፥ “ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ” ብለው ነበርና በእስራኤል ምድር ሁሉ ብረት ሠሪ አልተገኘም። 20 እስራኤልም ሁሉ ማረሻውንና ማጭዱን፥ መጥረቢያውንና መቈፈሪያውን ይስሉ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርዱ ነበር። 21 አዝመራውም ለአጨዳ ደርሶ ነበር። ለማረሻውና ለመቈፈሪያው ዋጋው ሦስት ሰቅል ነበር። መጥረቢያውንም ለማሳል፥ መውጊያውንም ለማበጀት ዋጋው ተመሳሳይ ነበር። 22 ስለዚህም በማኪማስ ጦርነት ጊዜ ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። 23 ከዚያም ጥቂቶች ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወደ ማኪማስ መተላለፊያ ወጡ። |