ዘካርያስ 9:8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ ምድሬን ዙሪያዋን ከብቤ እጠብቃለሁ፤ የወራሪ ኀይል መተላለፊያም አላደርጋትም። ሕዝቤ ምን ያኽል እንደ ተሠቃየ ስለ ተመለከትኩ ከእንግዲህ ወዲህ ጨቋኞች አይወሩአቸውም።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም እኔ ግን ቤቴን ከዘራፊ ኀይሎች እጠብቃለሁ፤ ጨቋኝ ከእንግዲህ ሕዝቤን አይወርስም፤ አሁን ነቅቼ እጠብቃለሁና። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሁንም በዓይኔ ስቃያቸውን አይቻለሁና ከዚህ በኋላ ጨቋኝ አይመጣባቸውም፤ በቤቴ ዙሪያ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ ከዘራፊዎች የሚጠብቅ እንዲሰፍር አደርጋለሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እኔም ማንም እንዳይሄድና እንዳይመለስ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ በቤቴ ዙሪያ ሰፈር አደርጋለሁ፣ አሁንም በዓይኔ አይቻለሁና ከዚህ በኋላ አስጨናቂ አያልፍባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እኔም ማንም እንዳይሄድና እንዳይመለስ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ በቤቴ ዙሪያ ሰፈር አደርጋለሁ፥ አሁንም በዓይኔ አይቻለሁና ከዚህ በኋላ አስጨናቂ አያልፍባቸውም። |
በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ነኮ የተባለው የግብጽ ንጉሥ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመርዳት ሠራዊቱን እየመራ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተጓዘ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም መጊዶ ላይ የግብጽን ሠራዊት ለማገድ ጦርነት ገጥሞ በዚያ ውጊያ ላይ ተገደለ፤
ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ።
ወፍ በጎጆዋ ላይ ክንፍዋን ዘርግታ በማንጃበብ ጫጩቶችዋን እንደምትጠብቅ፥ እኔ የሠራዊት አምላክ ኢየሩሳሌምን እጋርዳታለሁ፤ እጠብቃታለሁ፤ አድናታለሁ፤ ከችግር አወጣታለሁ።
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር መላውን ከተማና በእዚያም በሚሰበሰቡበት ሁሉ ላይ በቀን ጥቅጥቅ ያለ ደመናን፥ በየሌሊቱም በሚንበለበለው የእሳት ብርሃን ይልካል። የእግዚአብሔርም ክብር ከተማይቱን እንደ ትልቅ ድንኳን ሸፍኖ ይጠብቃታል።
ጽዮን ሆይ! ተነሺ፤ ንቂ! ኀይልሽን እንደ ልብስ ልበሺ! ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ! የተዋበ ልብስሽን ልበሺ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ያልተገረዙና በሥርዓት ያልነጹ ሰዎች ወደ ቅጥርሽ ውስጥ አይገቡም።
በፍትሕና በእውነት ላይ ትመሠረቺአለሽ፤ ግፍና ጭቈና ከአንቺ ይርቃል የሚያስፈራሽም የለም፤ ሽብርም ከአንቺ ይርቃል፤ ወደ አንቺም አይቀርብም።
ከእንግዲህ ወዲህ በምድርሽ የዐመፅ ድምፅ በድንበሮችሽም ጥፋት ወይም ውድመት አይሰማም፤ ነገር ግን ቅጥሮችሽን መዳን የቅጥር በሮችሽን ምስጋና ብለሽ ትጠሪአቸዋለሽ።
ስለዚህም ተመልሰው መጥተው በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በምሰጣቸውም የእህል፥ የወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ የበግና የቀንድ ከብት በረከት ሁሉ ተድላ ደስታ ያደርጋሉ፤ በቂ ውሃ እንዳገኘች የተክል ቦታ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ ወዲያም አያዝኑም።
ሕዝቤን እስራኤልን በሰጠኋቸው ምድር ላይ እተክላቸዋለሁ፤ ዳግመኛም ከዚያ ተነቅለው አይወጡም፤” ይህን የሚናገር እግዚአብሔር አምላካችሁ ነው።
በዚያን ጊዜ ፈረሶቻቸውን በፍርሃት አስጨንቃለሁ፤ ፈረሰኞችንም አሳብዳለሁ፤ የጠላቶቻቸውን ፈረሶች አሳውራለሁ፤ የይሁዳን ሕዝብ ግን በዐይኔ እየተመለከትኩ እጠብቃቸዋለሁ።
በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንደ ጋሻ መከታ እሆንላቸዋለሁ፤ ከእነርሱ እጅግ ደካማ የተባለው እንኳ የዳዊትን ያኽል ብርቱ ይሆናል፤ የዳዊት ልጆች እንደ እኔ እንደ እግዚአብሔር ወይም እንደ መላእክት ሆነው ሕዝቡን ይመራሉ።
ከእንግዲህ ወዲህ ደም ያለበትን ጥሬ ሥጋ ወይም ማንኛውንም የተከለከለ ምግብ አይበሉም፤ ከእነርሱ የተረፉት ከሕዝቤ ተቀላቅለው ከይሁዳ ነገድ እንደ አንድ ጐሣ ይሆናሉ፤ የዔቅሮን ሕዝብ ልክ እንደ ኢያቡሳውያን ከሕዝቡ ጋር ይቀላቀላሉ።
በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጽኑ መከራ በእርግጥ አይቼአለሁ፤ የጭንቀት ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ላድናቸው ወርጃለሁ፤ አሁንም ና! እኔ አንተን ወደ ግብጽ እልክሃለሁ።’