ሉቃስ 11:34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ በብርሃን የተሞላ ይሆናል፤ ዐይንህ ግን ታማሚ ከሆነ መላ ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ናት፤ ዐይንህ ጤናማ ስትሆን መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፤ ዐይንህ ታማሚ ከሆነች ግን መላ ሰውነትህ የጨለመ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው። ዐይንህ ጤናማ በሆነ ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ በብርሃን የተመላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ በሆነ ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ በጨለማ የተመላ ይሆናል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ነው፤ ዐይንህ ብሩህ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ነው፤ ዐይንህ ታማሚ ቢሆን ግን፤ ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል። |
ከአገልጋዬ በቀር ዕውር ማነው? ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ደንቆሮ ማነው? ራሱን ለእኔ እንዳስገዛው ያለው ዕውር ማን ነው? ወይም እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ ያለ ዕውር ማን ነው?
ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ለሚያስመስሉ፥ ጣፋጩን መራራ፥ መራራውን ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!
ቀጥሎም “እንዳያዩ፥ እንዳይሰሙና እንዳያስተውሉ በዓይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ ተመልሰው እንዳይፈወሱ ይህን ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ ጆሮው የተደፈነ፥ ዐይኑም የተጨፈነ እንዲሆን አድርግ” አለኝ።
ይህም የሚሆነው፥ ‘እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ኃጢአታቸው ይቅር እንዳይባልላቸው፥ ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤ መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’ ” በተባለው መሠረት ነው።
አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ።
ዐይናቸውን እንድትከፍትላቸውና ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድታወጣቸው ከሰይጣንም ግዛት ወደ እግዚአብሔር እንድትመልሳቸው አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በእኔ በማመናቸው ምክንያት የኃጢአታቸውን ይቅርታ ያገኛሉ፤ በተመረጡት መካከልም ርስትን ይካፈላሉ።’
የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም።
እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ሐሳብ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ያላችሁን ቅንና ንጹሕ የሆነ ታማኝነት ትተዋላችሁ ብዬ እፈራለሁ።
የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች ልብ አሳወረው፤ በዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል የሚያበራላቸውን ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው።
ክብር የሚገባው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔርን በይበልጥ ታውቁ ዘንድ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ።
እናንተ አገልጋዮች ሆይ! በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ታዘዙ፤ ለክርስቶስ በምታገለግሉት ዐይነት በልብ ቅንነት ታዘዙአቸው።
በባርነት ሥርዓት ያላችሁ! ለምድራዊ ጌቶቻችሁ በሁሉም ነገር ታዘዙ፤ የምትታዘዙትም እነርሱ ስለሚያዩአችሁና ሰውን ደስ ስለምታሰኙ ለታይታ ሳይሆን ጌታን በመፍራትና በልብ ቅንነት ይሁን።