ሆሴዕ 11:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እጆቻቸውን ይዤ በእግራቸው መረማመድን ያስተማርኳቸው እኔ ነበርኩ፤ ዕቅፍ አድርጌም ይዤአቸው ነበርኩ፤ እነርሱ ግን እኔ እንደምንከባከባቸው አላወቁም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኤፍሬምን እጁን ይዤ፣ እንዲራመድ ያስተማርሁት እኔ ነበርሁ፤ ነገር ግን የፈወስኋቸው እኔ እንደ ሆንሁ፣ እነርሱ አላስተዋሉም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ መራመድን አስተማርሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እኔም ኤፍሬምን ወደድሁት፤ በክንዴም ተቀበልሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ በእግሩ እንዲሄድ መራሁት፥ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። |
እንዲህም አላቸው፤ “በጥሞና ትእዛዞቼን ብታዳምጡና በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር በታዛዥነት ብታደርጉ፥ ኅጎቼንም ሁሉ ብትጠበቁ፥ በግብጻውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች በአንዱ እንኳ አልቀጣችሁም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
“ ‘እኔ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረግኹትንና ንስር ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ እንደምትሸከም እኔም እናንተን እስከዚህ ስፍራ እንዴት ወደ እኔ እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል፤
በዚያን ጊዜ ጨረቃ እንደ ፀሐይ ትደምቃለች፤ የፀሐይም ብርሃን ከቀድሞ ሰባት እጅ የበለጠ ይሆናል፤ የሰባት ቀን ብርሃን ያኽልም ድምቀት ይኖረዋል፤ ይህም ሁሉ የሚሆነው እግዚአብሔር ራሱ በሕዝቡ ላይ ያመጣባቸውን ቊስል ጠግኖ በሚፈውስበት ቀን ነው።
በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ያዳናቸው በመልእክተኛ ወይም በመልአክ አማካይነት ሳይሆን እርሱ በመካከላቸው በመገኘት ነው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ታደጋቸው፤ እርሱም በቀድሞ ዘመናት ሁሉ አንሥቶ ልጁን እንደሚሸከም ሰው ተንከባከባቸው።
ጠላቶቻችሁ ‘ጽዮን እንደ ተጣለች መቅረትዋ ነው፤ የሚጠነቀቅላትም የለም’ ቢሉም፥ እኔ ጤንነታችሁን እንደገና እመልስላችኋለሁ፤ ቊስላችሁንም እፈውሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሕዝቤን አለመታመን ፈውሼ፤ ወደ እኔ እመልሳቸዋለሁ ቊጣዬ ከእነርሱ ስለ ተመለሰ፥ እኔ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ፤
እርስዋ እህልን፥ የወይን ጠጅን፥ የወይራ ዘይትን የሰጠኋት፥ እኔ እንደ ሆንኩ ከቶ አልተገነዘበችም፤ እኔ ያበዛሁላትን ብርና ወርቅ “በዓል” ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት አቀረበች።
“ሕዝቤን እስራኤልን ለመፈወስና እንደገናም እንዲበለጽጉ ለማድረግ በፈለግሁ ጊዜ የሕዝቡ በደልና የሰማርያ ክፋት ጐልቶ ይታያል፤ እርስ በርሳቸው ሐሰት ይናገራሉ፤ ቤት እየሰበሩ ይሰርቃሉ፤ በቡድን በቡድን ሆነው በየመንገዱ ይዘርፋሉ።
እናንተ ወደዚህ ቦታ እስክትመጡ ድረስ አንድ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረ በዳው እንደ ተንከባከባችሁ አይታችኋል።’
አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዞች ስለ መጠበቅህ በልብህ ያለውን ሐሳብ ያውቅ ዘንድ አንተን ለመፈተን በዚህ በረሓ አርባ ዓመት ሙሉ በመከራ ውስጥ በማሳለፍ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ።