ዘዳግም 24:1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ እርስዋን የማይወድበትን ነገር በማግኘቱ ቢጠላት የፍች የምስክር ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ ያባርራታል፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍች ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባት በኋላ፥ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፥ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “አንድ ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፤ ከቤቱም ይስደዳት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፥ ከቤቱም ይስደዳት። |
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወንድ ሚስቱን ፈቶ እንደሚያባርር እኔ እናንተን ሕዝቤን ያባረርኩ ይመስላችኋልን? ይህስ ከሆነ የፍችው ደብዳቤ የት አለ? ሰው ልጆቹን ለባርነት እንደሚሸጥ እኔም እናንተን ለምርኮ አሳልፌ የሸጥኳችሁ ይመስላችኋልን? ከሆነስ ለማንኛውም አበዳሪዬ ሸጥኳችሁ? እናንተ ለምርኮ የተሰጣችሁት በኃጢአታችሁ ምክንያት ነው፤ የተሰደዳችሁትም በፈጸማችሁት በደል ነው።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ እርስዋም ከእርሱ ተለይታ ሌላ ወንድ ካገባች በኋላ እንደገና መልሶ ሊያገባት ይችላልን? ይህ ቢደረግማ ፈጽሞ ምድርን የሚያረክስ ይሆናል። እስራኤል ሆይ! አንቺ ግን ብዙ ጣዖቶችን ወደሽ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደገና ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽ።
እስራኤል እኔን ማምለክዋን ትታ የጣዖት አምልኮን ተከተለች፤ ይህንንም ስታደርግ የተውኳት መሆኔን ይሁዳ ተመልክታለች፤ እምነት የማይጣልባት የእስራኤል እኅት ይሁዳ ፍርሀት አላደረባትም፤ እርስዋም በበኩልዋ ጣዖት አምላኪ ሆናለች።
“እኔ የባልና የሚስትን መፋታት እጠላለሁ፤ ልብስን በፍትሕ አልባነት መሸፈንንም እጠላለሁ ሰውነቱን በልብስ እንደሚሸፍን በግፍ ሥራ የሚሸፍንን ሰው እጠላለሁ፤ ስለዚህ እምነተቢስ ከመሆን ተጠንቀቁ።” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።
“አንድ ሰው ሁለት ሚስቶችን አግብቶ አንደኛይቱን አፍቅሮ ሌላይቱን ባያፈቅርና ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ቢወልዱለት፥ ምናልባት የመጀመሪያው ልጅ የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፥
በተጨማሪም አንድ መቶ ጥሬ ብር መቀጫ አስከፍለው ገንዘቡን ለልጅትዋ አባት ይስጡት፤ ያ ሰው ድንግል የሆነችውን የአንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ስም አጒድፎአል፤ ከዚህም በቀር የእርሱ ሚስት ሆና ትኖራለች፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ሊፈታት አይገባም።
ለልጃገረዲቱ አባት ኀምሳ ጥሬ ብር ይክፈል፤ እርስዋም ለዚያ ሰው ሚስት ሆና ትኑር፤ አስገድዶ በመድፈር ከእርስዋ ጋር ስለ ተኛ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይችልም።
ሁለተኛውም ባል ስለሚጠላት የተፈታችበትን ምክንያት የሚገልጥ የፍች ደብዳቤ ጽፎ በመስጠት ከቤቱ ያባርራታል፤ ወይም ሁለተኛው ባልዋ ይሞት ይሆናል፤