ሚልክያስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እግዚአብሔር ለካህናቱ እንዲህ ይላል፦ “ካህናት ሆይ! አሁንም ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው። 2 ባታዳምጡ፥ ለስሜም ክብር ለመስጠት ቃሌን በልባችሁ ባታኖሩት መርገም እልክባችኋለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ ርግማን እለውጣለሁ፤ እኔን ማክበር በልባችሁ ውስጥ ስለሌለ በእርግጥ ይህን ሁሉ አደርግባችኋለሁ። 3 በእናንተ ምክንያት ልጆቻችሁን እቀጣለሁ፤ ለመሥዋዕት ያመጣችኋቸውን እንስሶች እበት በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ ከፊቴም አስወግዳችኋለሁ። 4 ከሌዊና ከተወላጆቹ ጋር ያለኝ ቃል ኪዳን ጸንቶ ይኖር ዘንድ ይህን ትእዛዝ እኔ የላክሁላችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ። 5 “የሰጠኋቸው ቃል ኪዳን የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው፤ እንዲሁም እኔን የማክበር ግዴታ አለባቸው፤ እነርሱም እኔን እየፈሩ ስሜን አክብረው ኖረዋል። 6 እነርሱ እውነትን ያስተምሩ ነበር፤ በአንደበታቸውም ስሕተት አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ተመላልሰዋል፤ በትምህርታቸው ብዙዎችን ከበደል መልሰዋል። 7 ካህን የሠራዊት አምላክ መልእክተኛ ስለ ሆነና ሕዝብም ከእርሱ ዕውቀትን ስለሚፈልግ የካህን አንደበት ዕውቀትን ጠብቆ ማኖር አለበት። 8 እናንተ ግን ከመንገድ ወጥታችሁ በትምህርታችሁ ብዙዎችን አሰናክላችኋል፤ ከሌዊ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል። 9 የእኔን ሥርዓት ባለመከታተል በሕግ ጉዳይ አድልዎ ስለምትፈጽሙ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አደርጋችኋለሁ።” የሕዝቡ በእግዚአብሔር አለመታመን 10 ለሁላችንም አንድ አባት ያለን አይደለምን፤ የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ ለምን የቀድሞ አባቶቻችንን ቃል ኪዳን በማፍረስ እርስ በርሳችን እምነተቢሶች እንሆናለን? 11 የይሁዳ ሕዝብ እምነተቢስ ሆኖአል፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም አጸያፊ የርኲሰት ሥራ ፈጽመዋል፤ ይህም የሆነው ጣዖት አምላኪዎች የሆኑ የባዕድ ሴቶችን በማግባት ይሁዳ እግዚአብሔር የሚወደውን ቤተ መቅደስ ስላረከሰ ነው። 12 ይህን የሚያደርገውን ሰው ለሠራዊት አምላክ መሥዋዕት ቢያቀርብም እንኳ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ያጥፋው። 13 እንዲህም ታደርጋላችሁ፦ እግዚአብሔር መሥዋዕታችሁን ስለማይቀበለው የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ፥ በለቅሶና በሐዘን ትሸፍናላችሁ። 14 “ስለምን መሥዋዕታችንን አይቀበልም?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፤ እግዚአብሔር መሥዋዕታችሁን የማይቀበለው የቃል ኪዳን ጓደኞቻችሁ ለሆኑት ለወጣትነት ሚስቶቻችሁ ታማኝነታችሁን ስላፈረሳችሁ ነው፤ በእናንተም መካከል እግዚአብሔር ምስክር ነበር። 15 ታዲያ እግዚአብሔር እናንተና ሚስቶቻችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ እንዲኖራችሁ አድርጎ አልነበረምን? በዚህስ የእርሱ ዓላማ ምን ነበር? ዋና ዓላማው የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሆኑ ልጆችን እንድትወልዱ በመፈለግ ነበር፤ ስለዚህ ከእናንተ እያንዳንዱ ለሚስቱ የገባውን ቃል ኪዳን አያፍርስ። 16 “እኔ የባልና የሚስትን መፋታት እጠላለሁ፤ ልብስን በፍትሕ አልባነት መሸፈንንም እጠላለሁ ሰውነቱን በልብስ እንደሚሸፍን በግፍ ሥራ የሚሸፍንን ሰው እጠላለሁ፤ ስለዚህ እምነተቢስ ከመሆን ተጠንቀቁ።” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። የፍርድ ቀን መቅረቡ 17 በቃላችሁ እግዚአብሔርን አሰልችታችሁታል፤ “እርሱን ያሰለቸነው በምንድን ነው?” ትላላችሁ፤ እርሱን ያሰለቻችሁት፦ “ክፉ አድራጊ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፤ እግዚአብሔርንም ያስደስተዋል” በማለት ወይም “የፍትሕ አምላክ የት አለ?” ብላችሁ በመጠየቅ ነው። |