Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 “የእስራኤላዊ ወገንህ ንብረት የሆነ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ሲባዝን ብታገኝ ዝም ብለህ አትለፈው፤ ወደ ባለቤቱ መልሰህ ውሰድለት፤

2 ነገር ግን ባለቤቱ የሚኖርበት ቦታ ሩቅ ቢሆን፥ ወይም ባለቤቱ ማን እንደ ሆነ ካላወቅህ እንስሳውን ወደ ቤትህ ውሰደው፤ እርሱን ሊፈልግ በሚመጣበት ጊዜ ለባለቤቱ ስጠው፤

3 እንዲሁም አህያም ሆነ ልብስ ወይም ማንኛውንም ሌላ ነገር ከእስራኤላዊ ወገንህ ጠፍቶ ብታገኝ ችላ ሳትል መልሰህ ስጠው።

4 “የእስራኤላዊ ወገንህ አህያ ወይም በሬ መንገድ ላይ ወድቆ ብታይ ዝም ብለህ አትለፍ፤ ቆሞ እንዲሄድ እንስሳውን በማንሣት እርዳው።

5 “እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደዚህ የሚያደርጉትን ስለሚጠላ ሴቶች የወንዶችን፥ ወንዶችም የሴቶችን ልብስ አይልበሱ።

6 “አንዲት ወፍ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ ጫጩቶችዋንም ሆነ እንቊላሎችዋን ዐቅፋ የተቀመጠችበትን ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ወፍ ከነጫጩቶችዋ አትውሰድ፤

7 ጫጩቶቹን መውሰድ ትችላለህ፤ እናቲቱን ወፍ ግን እንድትበር ልቀቃት፤ ይህን ብታደርግ ሀብታም ሆነህ ለረጅም ዘመን ትኖራለህ።

8 “አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ በጣራው ክፈፍ ዙሪያ መከታ አድርግለት፤ አለበለዚያ አንድ ሰው ከጣራው ላይ ቢወድቅ ለደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ።

9 “በወይን ተክልህ ውስጥ ሌላ ዘር አትዝራ፤ ይህን ብታደርግ በወይኑ ፍሬም ሆነ በሌላው ሰብል መጠቀም አትችልም።

10 “በሬንና አህያን በአንድ ቀንበር ጠምደህ አትረስ።

11 “ሱፍና በፍታ ተቀላቅሎ አብሮ የተሠራ ልብስ አትልበስ።

12 “በልብስህ ላይ በአራቱም ማእዘን ዘርፍ አብጅለት።


የጋብቻ ግንኙነትን በንጽሕና ስለ መጠበቅ

13 “አንድ ሰው ሚስት ካገባ በኋላ ቢጠላትና፥

14 ‘ይህችን ሴት አግብቼ ክብረ ንጽሕናዋን አላገኘሁም’ ብሎ በሐሰት ክስ ስምዋን ቢያጠፋ፥

15 የልጅትዋ ወላጆች ልጅቱ ድንግል መሆንዋን የሚያረጋግጥላትን ማስረጃ አምጥተው በከተማይቱ ሸንጎ ለሚገኙት መሪዎች ያሳዩ።

16 የልጅቱም አባት እንዲህ ብሎ ያስረዳ፦ ‘እኔ ሴት ልጄን ለዚህ ሰው ድሬለት ነበር፤ እነሆ፥ አሁን እርሱ የጠላት መሆኑን ገልጦአል።

17 የልጅህን ድንግልና የሚያመለክት ማስረጃ አላገኘሁም ብሎ የልጄን ስም አጐደፈ፤ ለልጄ የድንግልናዋ ማረጋገጫ ምልክት ይኸውና!’ በማለት በመሪዎቹ ፊት የማስረጃውን ሻሽ ይዘርጋ።

18 የከተማይቱም መሪዎች ባልየውን ወስደው በመግረፍ ይቅጡት።

19 በተጨማሪም አንድ መቶ ጥሬ ብር መቀጫ አስከፍለው ገንዘቡን ለልጅትዋ አባት ይስጡት፤ ያ ሰው ድንግል የሆነችውን የአንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ስም አጒድፎአል፤ ከዚህም በቀር የእርሱ ሚስት ሆና ትኖራለች፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ሊፈታት አይገባም።

20 “ነገር ግን ክሱ እውነት ሆኖ ቢገኝና ድንግል ስለ መሆንዋ የሚያስረዳ ነገር ባይኖር፥

21 በአባትዋ ቤት እያለች አሳፋሪ የሆነውን የዝሙት ሥራ በእስራኤል መካከል ስለ ሠራች ወደ አባትዋ ቤት ደጃፍ ይውሰዱአት፤ በዚያም እርስዋ የምትኖርበት ከተማ ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሉአት፤ በዚህም ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ።

22 “አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ ሁለቱም ይገደሉ። በዚህም ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ከእስራኤል አስወግዱ።

23 “አንድ ሰው በአንዲት ከተማ ለሌላ ሰው ከታጨች ድንግል ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥

24 ሁለቱንም ከከተማይቱ ወደ ውጪ አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉ፤ ልጃገረዲቱ መሞት የሚገባት ሰው ሊሰማ በሚችልበት ከተማ ውስጥ እያለች ርዳታ እንዲደረግላት የጩኸት ድምፅ ባለማሰማትዋ ነው፤ ሰውየውም የሚሞትበት ምክንያት ለሌላ ሰው ከታጨች ልጃገረድ ጋር በመተኛት ሕግን በማፍረሱ ነው፤ በዚህ ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ።

25 “አንድ ሰው ለሌላ ሰው የታጨችውን ልጃገረድ ከከተማዋ ውጪ በዋለችበት አግኝቶ በመድፈር ድንግልናዋን ቢገሥ ብቻውን ይገደል።

26 እርስዋ ለሞት የሚያበቃ በደል ስላልፈጸመች በልጃገረዲቱ ላይ ምንም ነገር አይድረስባት፤ ይህ ፍሬ ነገር አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ አደጋ ጥሎ በመግደል የሚፈጽመውን ወንጀል ይመስላል።

27 ይህም የሚሆንበት ምክንያት ያ ሰው ያቺን ለሌላ ሰው ታጭታ የነበረች ልጃገረድ ከከተማ ውጪ በዋለችበት አግኝቶአት ስለ ነበርና ርዳታ ለማግኘት ብትጮኽም የሚደርስላት በማጣትዋ ነው።

28 “አንድ ሰው ለሌላ ሰው ያልታጨችውን ልጃገረድ አግኝቶ በመውሰድ ሲደርስባት ቢያዝ፥

29 ለልጃገረዲቱ አባት ኀምሳ ጥሬ ብር ይክፈል፤ እርስዋም ለዚያ ሰው ሚስት ሆና ትኑር፤ አስገድዶ በመድፈር ከእርስዋ ጋር ስለ ተኛ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

30 “ማንም ሰው የአባቱ ሚስት ከሆነችው ከማንኛይቱም ሴት ጋር ግንኙነት በማድረግ አባቱን አያሳፍር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos