ቈላስይስ 3:8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አሁን ግን ቊጣን፥ ንዴትን፥ ተንኰልን፥ ስም ማጥፋትን ከእናንተ አስወግዱ፤ የሚያሳፍር ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትን፣ ስድብንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሁን ግን እናንተ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አሁንም ቍጣንና ብስጭትን፥ ክፋትንና ስድብን፥ የሚያሳፍረውንም ነገር ተዉ፤ ከንቱ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ |
እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል።
እናንተ አሁንም ገና ሥጋውያን ናችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ስለምትቀናኑና ስለምትከራከሩ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? የምትሠሩትስ እንደ ተራ ሰው አይደለምን?
እኔ ወደዚያ በምመጣበት ጊዜ ምናልባት ልትሆኑ እንደምፈልገው ሳትሆኑ፥ እኔም እናንተ እንደምትፈልጉት ሳልሆን እንገናኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ፤ እንዲሁም በእናንተ ዘንድ ጥል፥ ቅናት፥ ቊጣ፥ ራስ ወዳድነት፥ የሰው ስም ማጥፋት፥ ሐሜት፥ ትዕቢትና ሁከት ይኖሩ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ።
ይልቅስ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ እንጂ የሚያስቀይምና የሞኝነት አነጋገር፥ ወይም የፌዝን ነገር መናገር አይገባችሁም፤ እንዲህ ያለ ነገር ለእናንተ ተስማሚ አይደለም።
ስለዚህ በእናንተ የሚገኙትን የምድራዊ ሕይወት ምኞቶች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም “ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ፍትወት፥ ክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀት” ናቸው።
ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን የሰደብኩና ያሳደድኩ፥ ያዋረድኩም ብሆን፤ እርሱ ምሕረት አደረገልኝ፤ እርሱም ይህን ምሕረት ያደረገልኝ እኔ ይህን ሁሉ ያደረግኹት ባለማወቅና ባለማመን ስለ ነበረ ነው።
ከእነርሱ መካከል ሄሜኔዎስና እስክንድር ይገኛሉ፤ እነርሱ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ከመናገር መቈጠብን እንዲማሩ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁ።
እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉን እኛ እንደ ሸክም የሆነብንን ነገር ሁሉ በእኛ ላይ የተጣበቀብንን ኃጢአት አስወግደን በፊታችንም ያለውን የሩጫ እሽቅድድም በትዕግሥት በመጽናት እንሩጥ።
በስሕተት ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አምልጠው ከመጡ ገና ብዙ ያልቈዩትን ሰዎች ከንቱ የሆነ የዕብሪት ቃል በመናገር፥ በሥጋዊ ፍትወትና በሴሰኛነት በማባበል ያታልሉአቸዋል።
የአሳፋሪ ድርጊታቸውን ዐረፋ የሚደፍቁ፥ እንደ ተቈጣ የባሕር ማዕበል ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም እንደሚጠብቃቸውና፥ እንደሚንከራተቱ ኮከቦች ናቸው።
ሰዎች በታላቅ ግለት ተቃጠሉ፤ በእነዚህ መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ንስሓ አልገቡም፤ እርሱንም አላከበሩም።