ምሳሌ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ጥልና ክርክር በበዛበት ቤት በታላቅ ግብዣ ላይ ከመገኘት ይልቅ ሰላም ባለበት ቤት ደረቅ የዳቦ ቊራሽ መመገብ ይሻላል። 2 የጌታው ልጅ ወራዳ ከሆነ ብልኅ አገልጋይ በጌታው ልጅ ላይ የበላይነት ይኖረዋል፤ ከወንድማማቾቹም ጋር ርስት ተካፋይ ይሆናል። 3 ወርቅና ብር በእሳት እንደሚፈተን እግዚአብሔርም የሰውን ልብ ይፈትናል። 4 ክፉ ሰዎች ክፉ ነገርን ይሰማሉ፤ ሐሰተኞችም ሐሰትን ያዳምጣሉ። 5 በድኾች ብታፌዝ የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን እንደ ሰደብክ ይቈጠራል፤ በሌላው ሰው ላይ በሚደርሰው መከራ ብትደሰት አንተም ትቀጣለህ። 6 የሸመገሉ ሰዎች በልጅ ልጆቻቸው እንደሚመኩ ልጆችም በአባቶቻቸው ይመካሉ። 7 ሞኝ ሰው ቁም ነገር አይናገርም፤ ከጨዋ ሰው ግን የውሸት ንግግር አይጠበቅም። 8 አንዳንድ ሰዎች ጉቦ እንደ አስማት የሚሠራ ይመስላቸዋል፤ ጉቦ በመስጠትም ሁሉ ነገር ይሳካልናል ብለው ያምናሉ። 9 የበደለን ሰው ይቅር የሚል ወዳጅነትን ያጸናል፤ በደልን መላልሶ የሚናገር ሰው ግን የቅርብ ወዳጆቹን ያጣል። 10 ሞኝ መቶ ጊዜ ተገርፎ ከሚማረው ይልቅ አስተዋይ ሰው ከአንድ ጊዜ በማይበልጥ ተግሣጽ የሚማረው ይበልጣል። 11 ክፉ ሰው ሁልጊዜ ዐመፀኛ ነው፤ ስለዚህ ምሕረት የሌለው መልእክተኛ ይላክበታል። 12 ሞኝን የሞኝነት ሥራ ሲሠራ ከመገናኘት ይልቅ ልጆችዋ የተነጠቁባትን ድብ መገናኘት ይሻላል። 13 ደግ ነገር ተደርጎለት ክፉ ነገር የሚመልስ ክፉ ነገር ዘወትር ከቤቱ አይለይም። 14 የጥል መነሻ መፍረስ እንደ ጀመረ ግድብ ነው፤ ስለዚህ ጥል ከማስከተሉ በፊት ክርክርን አቁም። 15 በንጹሕ ሰው ላይ መፍረድ፥ ወይም በደለኛውን ንጹሕ ማድረግ ሁለቱም እግዚአብሔር የሚጸየፋቸው ድርጊቶች ናቸው። 16 ሞኝ የተፈጥሮ ማስተዋል ስለሌለው ገንዘቡን ጥበብን ለማግኘት ቢያውል ምንም አይጠቅመውም። 17 ወዳጅ ምን ጊዜም ቢሆን ወዳጁን ይወዳል፤ ወንድም የሚወለደው የወንድሙን ችግር ለመካፈል ነው። 18 ማስተዋል የጐደለው ሰው ለሌላ ሰው ዋስ ይሆናል፤ ራሱንም ተያዥ አድርጎ ይሰጣል። 19 ኃጢአትን የሚወድ ጠብን ይወዳል፤ ከፍ ብሎ እንደ ተሠራ ደጃፍ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሰው ውድቀትን ይጋብዛል። 20 ጠማማ ልብ ያለው አይበለጽግም፤ አንደበቱ አታላይ የሆነ ሰው ችግር ላይ ይወድቃል። 21 የሰነፍ ልጅ አባት ከሐዘንና ከብስጭት በቀር ምንም ደስታ የለውም። 22 ደስተኛነት ለልብ መልካም መድኃኒት ነው፤ የመንፈስ ሐዘንተኛ መሆን ግን አጥንትን ይሰብራል። 23 ክፉ ሰው ፍርድን ለማጣመም፥ በምሥጢር ጉቦ ይቀበላል። 24 አስተዋይ ሰው ወደ ጥበብ ያዞራል፤ የሞኝ ዐይኖች ግን በብዙ አቅጣጫ ይባዝናሉ። 25 ሰነፍ ልጅ አባቱን በሐዘን ላይ ይጥላል፤ በእናቱም ላይ መራራ ጸጸት ያመጣል። 26 ንጹሑን ሰው መቀጫ ማስከፈል፥ ወይም ጨዋውን ሰው ማስገረፍ ተገቢ አይደለም። 27 ንግግሩን የሚቈጥብ ዐዋቂ ነው፤ የረጋ መንፈስ ያለውም ሰው አስተዋይ ነው። 28 ሞኝ ዝም ሲል ጥበበኛ ይመስላል፤ ምንም ሳይናገር ቢቀር እንደ ብልኅ ይቈጠራል። |