ሆሴዕ 10:12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የመሻት ዘመን ነውና ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ሰብስቡ፥ ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እኔም ‘እንግዲህ ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤ ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፤ የማይለዋወጥ ፍቅርን ሰብስቡ፤ እነሆ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው! እኔም መጥቼ ፍትሕን አሰፍንላችኋለሁ’ አልኩ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ለእናንተ ጽድቅን ዝሩ፤ የሕይወት ፍሬን ሰብስቡ፤ የጥበብንም ብርሃን ለራሳችሁ አብሩ፤ የጽድቃችሁ መከር እስኪደርስ እግዚአብሔርን ፈልጉት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ። |
በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፥ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይሰማራሉ፤
ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ ጌታንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው!
እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፥ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ ጌታ ፈጥሬዋለሁ።
በዚያም ወራት በዚያም ጊዜ፥ ይላል ጌታ፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ፥ እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም ጌታን ይፈልጋሉ።
እኛም እንወቅ፤ ጌታን ለማወቅ እንትጋ፤ እንደ ንጋትም መገለጡ እርግጥ ነው፤ እንደ ዝናብ ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ በልግ ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።”
በዮሴፍ ቤት ላይ እንደ እሳት በድንገት እንዳይቀጣጠል፥ በቤቴልም ላይ የሚያጠፋው ሳይኖር እንዳይበላት፥ ጌታን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮበብ የፈጠረ፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጥ፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልም፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸው እርሱ፥ ስሙ ጌታ ነው።