ምሳሌ 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የሐሰት ሚዛን በጌታ ፊት አስጸያፊ ነው፥ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል። 2 ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፥ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። 3 ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፥ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች። 4 በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፥ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። 5 የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፥ ክፉ ግን በክፋቱ ይወድቃል። 6 ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፥ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ። 7 ክፉ ሰው በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል። 8 ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ክፉ ግን የእርሱን ቦታ ይወስዳል። 9 እኩይ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፥ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ። 10 በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በክፉዎችም ጥፋት እልል ትላለች። 11 በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፥ በክፉዎች አፍ ግን ትገለበጣለች። 12 ወዳጁን የሚንቅ ልበ ጐደሎ ነው፥ አስተዋይ ሰው ግን ዝም ይላል። 13 ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፥ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል። 14 መልካም ምክር በሌለበት ሕዝብ ይወድቃል፥ በአማካሪዎች ብዛት ግን ዋስትና ይገኛል። 15 ለእንግዳ ሰው የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፥ ዋስ መሆንን የሚጠላ ግን ይድናል። 16 ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ኃያላንም ሀብትን ያገኛሉ።። 17 ቸር ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፥ ጨካኝ ግን ራሱን ይጐዳል። 18 ክፉ ሰው የሐሰት ደመወዝ ያገኛል፥ ጽድቅን የሚዘራ ግን የታመነ ዋጋ አለው። 19 በጽድቅ የሚጸና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፥ ክፋትን የሚከተል ግን ወደ ሞት ይሄዳል። 20 ልበ ጠማሞች በጌታ ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው፥ በመንገዳቸው ፍጹማን የሆኑ ግን የተወደዱ ናቸው። 21 ክፉ ሰው በእርግጠኛነት ሳይቀጣ አይቀርም፥ የጻድቃን ዘር ግን ይድናል። 22 በዐሣማ አፍንጫ ላይ የወርቅ ቀለበት፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴት። 23 የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው፥ የክፉዎች ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው። 24 በልግስና የሚሰጥ ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፥ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፥ ይደኸያልም። 25 በረከትን የምታካፍል ነፍስ ትጠግባለች፥ ውሃን የሚያጠጣ እርሱ ደግሞ ይረካል። 26 እህልን የሚደብቅ ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፥ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው። 27 መልካምን ተግቶ የሚሻ ደስታን ይፈልጋል፥ ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል። 28 በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል፥ ጻድቃን ግን እንደ ቅጠል ይለመልማሉ። 29 ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፥ አላዋቂም ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል። 30 የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚማርክ እርሱ ጠቢብ ነው። 31 እነሆ፥ ጻድቅ በምድር ላይ ፍዳውን የሚቀበል ከሆነ፥ ይልቁንስ ክፉዎችና ዓመፀኞችስ እንዴት ይሆኑ! |