ዘዳግም 26:13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል፦ ‘ከቤቴ የተቀደሰውን ድርሻ ወስጄ ባዘዝከን ትእዛዞች ሁሉ መሠረት ለሌዋውያን፥ ለመጻተኞች፥ ለሙት ልጆችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ሰጥቼአለሁ፤ ከትእዛዞችህም አልተላለፍኩም፤ የዘነጋሁትም ነገር የለም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያ በኋላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲህ በል፤ “በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት የተቀደሰውን ክፍል ከቤቴ አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከዚያ በኋላ ለጌታህ እግዚአብሔር እንዲህ በል፦ ‘ከቤቴ የተቀደሰውን ድርሻ ወስጄ በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት ለሌዋዊው፥ ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል፦ የተቀደሰውን ነገር ከቤቴ ለይች ለሌዋዊው፥ ለመጻተኛውም፥ ለድሀ-አደጉም፥ ለመበለቲቱም እንዳዘዝኸኝ ትእዛዝ ሁሉ ሰጥቼአለሁ፤ ትእዛዝህን ምንም አላፈረስሁም፤ አልረሳሁምም፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል፦ የተቀደሰውን ነገር ከቤቴ ወስጄ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም እንዳዘዝኽኝ ትእዛዝ ሁሉ ሰጥቼአለሁ፤ ትእዛዝህን ምንም አላፈረስሁም፥ አልረሳሁምም፤ |
የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም።
በከተሞቻችሁ የሚኖሩ ከእናንተ ጋር የተካፈሉት ርስት የሌላቸው ሌዋውያን፥ የውጪ አገር ስደተኞች፥ እናትና አባት የሌላቸው የሙት ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መጥተው ይብሉ፤ ይህን ሁሉ ብታደርጉ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምትሠሩት ነገር ሁሉ ይባርካችኋል።
“በሦስተኛው ዓመት ማለት ዐሥራት በምታወጣት ዓመት ዐሥራትህን ሁሉ አጠናቅቀህ ከሰበሰብክ በኋላ በከተማህ ለሚገኙ ለሌዋውያን፥ ለመጻተኞች፥ ለሙት ልጆችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ሰጥተህ ጠግበው እንዲበሉ አድርግ።
በሞት ሐዘን ጊዜ ከእርሱ አልበላሁም፤ ንጹሕ ባልሆንኩበት ጊዜ ከእርሱ ምንም አላነሣሁም፤ ስለ ሞተ ሰው ለሚቀርብ መባ ከእርሱ ምንም አላቀረብኩም፤ ባዘዝከኝ መሠረት የአንተን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ።
በእናንተ በአማኞች መካከል በነበርንበት ጊዜ እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ሕይወት እንደ ኖርን እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክር ነው፤