ቈላስይስ 1:9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እናንተ በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ከመጸለይና እግዚአብሔርን ከመለመን አላቋረጥንም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ስለዚህ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን በመንፈሳዊ ጥበብና ማስተዋል ሁሉ የፈቃዱን እውቀት እንድትሞሉ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስለዚህም እኛ ዜናችሁን ከሰማን ጀምሮ፥ በፍጹም ጥበብና በፍጹም መንፈሳዊ ምክር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅን ትፈጽሙ ዘንድ፥ ስለ እናንተ መጸለይንና መለመንን አልተውንም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ |
መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ አእምሮአችሁን በማደስ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉት።
የምትታዘዙትም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ እንደሚፈጽሙ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ሆናችሁ ነው እንጂ ሰውን ደስ ለማሰኘት ብላችሁ ለታይታ አይሁን።
እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው።
የክርስቶስ ቃል በሙላት በልባችሁ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመሰገናችሁ ዘምሩ።
የእናንተ ወገን የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ኤጳፍራም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በመንፈሳዊ ሕይወት በማደግ ጸንታችሁ እንድትቆሙና የእግዚአብሔርንም ፈቃድ በሙሉ እንድትፈጽሙ እርሱ ስለ እናንተ በጸሎቱ ዘወትር ይጸልያል።
በአምላካችንና በአባታችን ፊት እምነታችሁ የሚሠራውን፥ ለፍቅር የምታደርጉትንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቃችሁን ሳናቋርጥ እናስታውሳለን።
ይህን በማሰብ ስለ እናንተ ሳናቋርጥ የምንጸልየው አምላካችን ለጥሪው ብቁዎች እንዲያደርጋችሁና መልካም ለማድረግ ያላችሁን ፈቃድና የእምነት ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ነው።
ፈቃዱን ለመፈጸም እንድትበቁ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሰኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለኢየሱስ ክርስቶስም ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጐደለው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን ይለምን፤ እግዚአብሔርም ይሰጠዋል፤ እርሱ ምንም ቅር ሳይለው ለሁሉም በልግሥና የሚሰጥ ቸር አምላክ ነው።
ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሚገኘው ጥበብ በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ ታዛዥ፥ ምሕረት አድራጊ፥ ጥሩ ፍሬ የሞላበት፥ አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣና እውነተኛውን አምላክ እንድናውቅ አስተዋይ ልቡና እንደ ሰጠን እናውቃለን በልጁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ኅብረት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።