ሐዋርያት ሥራ 12:17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመልክቶ ጌታ ከወህኒ ቤት እንዴት እንዳስወጣው አወራላቸውና “ይህን ነገር ለያዕቆብና ለቀሩት ምእመናን ንገሩ” አላቸው። ተለይቶአቸውም ወደ ሌላ ቦታ ሄደ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እርሱም ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ፣ ጌታ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው አስረዳቸው፣ “ስለ ሁኔታው ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው፤ ከዚያም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና “ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞቹ ንገሩ፤” አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመለከታቸው፤ ከወኅኒ ቤትም እግዚአብሔር እንደ አወጣው ነገራቸው፤ “ይህንም ለያዕቆብና ለወንድሞች ሁሉ ንገሩ” አላቸው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና፦ “ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞቹ ንገሩ” አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። |
በአንድ ከተማ መከራ ሲያበዙባችሁ፥ ወደ ሌላው ሽሹ፤ በእውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞች ሁሉ አታዳርሱም።
ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ።
ዘካርያስ ከቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ከሰዎቹ ጋር መነጋገር አልቻለም፤ ስለዚህ እነርሱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ራእይ የታየው መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ በእጁ እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በዚህም ሁኔታ ዱዳ ሆኖ ቈየ።
ከዚያን ወዲያ ኢየሱስ በአይሁድ መካከል በግልጥ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ ወጥቶ በበረሓ አጠገብ ወዳለችው ኤፍሬም ወደምትባለው ከተማ ሄደ፤ እዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቈየ።
አንዳንድ የአይሁድ ወገኖች እስክንድር የተባለውን ሰው ከሕዝቡ ገፋፍተው ወደ ፊት አቀረቡት፤ ከሕዝቡም መካከል አንዳንዶቹ በደንብ እንዲከራከርላቸው መከሩት፤ እስክንድርም ሕዝቡ ጸጥ እንዲል በእጁ ጠቀሰና የመከላከያ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጀ።
እንዲናገር በፈቀደለት ጊዜ ጳውሎስ በደረጃ ላይ ቆሞ ሕዝቡ ዝም እንዲል በእጁ ጠቀሰ፤ ሕዝቡ ጸጥ ባለ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤
በሮም ያሉ ምእመናን ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዮስ ገበያና “ሦስት ማደሪያዎች” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ፤ ጳውሎስ እነርሱን ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነና ተጽናና።
ያዕቆብ የላካቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ አንጾኪያ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ መካከል ከአመኑት ጋር አብሮ ይበላ ነበር፤ እነርሱ ከመጡ በኋላ ግን “ከአሕዛብ ወገን ያመኑት መገረዝ አለባቸው” የሚሉትን ቡድኖች በመፍራት ወደ ኋላ አፈግፍጎ ከአሕዛብ ተለየ።
እንደ ምሰሶ መስለው የሚታዩት መሪዎች ያዕቆብና ጴጥሮስ ዮሐንስም እግዚአብሔር በጸጋ ይህን ልዩ የአገልግሎት ዕድል እንደ ሰጠኝ በተረዱ ጊዜ ለእኔና ለበርናባስ የመተባበራቸው ምልክት የሆነውን ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ እኛ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ እነርሱም ወደ አይሁድ እንዲሄዱ ተስማሙ።
በዓለም ሁሉ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ከሆነው ከያዕቆብ የተላከ መልእክት፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን።