ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ተረፈ ባሮክ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ያንጊዜም ኤርምያስና ባሮክ፥ “የዚህ ነገር ምልክት በእውነት እንደ ተገኘ ዛሬ ዐወቅን” ብለው አለቀሱ። 2 ኤርምያስም፥ “እግዚአብሔርን አንዲት ነገርን እስክለምነው ድረስ ከተማዋን ሁሉ እንዳታጠፉ እለምናችኋለሁ” ብሎ መላእክትን ማለዳቸው። 3 ጌታም፥ “ከወዳጄ ከኤርምያስ ጋራ እስክነጋገር ድረስ ከተማዪቱን አታጥፉ” ብሎ ለመላእክት ነገራቸው። 4 ኤርምያስም ያንጊዜ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ ከአንተ ጋር እናገር ዘንድ እዘዘኝ” ብሎ ተናገረ፤ ጌታም፥ “ወዳጄ ኤርምያስ ሆይ፥ የምትወድደውን ተናገር” አለው። 5 ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ይቺን ከተማ በጠላትዋ እጅ አሳልፈህ እንደምትሰጣት የባቢሎንም ሕዝብ እንደሚይዟት እነሆ፥ ዛሬ ዐወቅሁ። 6 ተሰውረን ስለምናገለግልባቸው ንዋያተ ቅድሳት ምን አደርግ ዘንድ ትወድዳለህ? በላያቸውስ ምን አደርግ ዘንድ ትወድዳለህ?” 7 ጌታም አለው፥ “እነርሱን ወስደህ ለምድር አደራ ስጣት፤ አንቺ ምድር በውኆች ላይ የፈጠረሽ፥ በሰባቱም ማኅተም ያተመሽ የፈጣሪሽ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተሽ ጌጥሽን ተቀበዪ፤ ተወዳጁም እስኪመጣ ድረስ ገንዘብሽን ጠብቂ በላት።” 8 ኤርምያስም እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ ሕዝቡን ብዙ ዘመን ለጠበቃቸው፥ እኔን ባሪያህ ኤርምያስንም ከሀገሩ ሰው ሁሉ ይልቅ ለጠበቀኝ ለኢትዮጵያዊው ለአቤሜሌክ የማደርገውን ግለጥልኝ። 9 እርሱ ከረግረግ ጕድጓድ አወጣኝ፤ እንዳያዝን የከተማዋን ጥፋት ያይ ዘንድ አልወድለትም።” 10 ጌታም ለኤርምያስ እንዲህ አለው፥ “ወደ አግሪጳስ ወይን ቦታ በዚህ ተራራ ጎዳና አቤሜሌክን ላከው፤ ሕዝቡን ወደ ሀገራቸው እስክመልሳቸው ድረስ እኔ እሰውረዋለሁ። 11 አንተም ኤርምያስ ወደ ባቢሎን ሀገር እስክትደርስ ድረስ ከሕዝቡ ጋራ ወደ ግብፅ ሂድ፤ ወደ ሀገራቸውም እስክመልሳቸው ድረስ ስታስተምራቸው ኑር። 12 ባሮክን ግን በዚያ በኢየሩሳሌም ተወው፤” ጌታም ይህን ሁሉ ነገር ለኤርምያስ ነግሮት ከኤርምያስ ዘንድ ወደ ሰማይ አልፎ ወጣ። 13 ባሮክና ኤርምያስም ወደ ቤተ መቅደስ ገቡ፤ የሚያገለግሉበትንም ዕቃ ሁሉ ጌታ እንዳዘዛቸው ለምድር ሰጧት፤ ምድርም ያንጊዜ ተቀብላ ዋጠችው። 14 ሁለቱም ሁሉ ተቀምጠው አለቀሱ፤ በማግሥቱም በነጋ ጊዜ ኤርምያስ አቤሜሌክን፥ “ሙዳዩን ይዘህ ወደ አግሪጳስ የወይን ቦታ በተራራው ጎዳና ሂድ፤ የእግዚአብሔር ረድኤት፥ ጌትነቱም በአንተ ራስ አድሯልና ለታመሙ ወገኖች ጥቂት በለስን አምጣ” ብሎ ላከው። 15 እርሱም እንዳዘዘው ሄደ፤ በማግሥቱም በነጋ ጊዜ የከለዳውያን ሠራዊት ከተማዪቱን ከበቧት፤ ታላቁም መልአክ መለከቱን ነፋ። 16 እርሱም፥ “የከለዳውያን ሠራዊት፥ ግቡ፤ እነሆ፥ በሮቹ ይከፈቱላችኋል” አለ። 17 ያንጊዜም ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋር ገብቶ ሕዝቡን ሁሉ ማረከ። 18 ያንጊዜም ኤርምያስ የቤተ መቅደሱን መክፈቻ ይዞ ከከተማ ወደ ውጭ ወጣ። 19 ይህንም መክፈቻ “ፀሐይ፥ የእግዚአብሔርን ቤት መክፈቻ ተቀበል” ብሎ በፀሐይ ፊት ጣለው። 20 “ኀጢአታችንን እኛ እየተከባከብናት ስለ ተገኘን ከተወለድን ጀምሮ እርሱን ለመጠበቅ አይገባንምና እግዚአብሔር የእርሱን ነገር እስከሚነግርህ እስከ ብዙ ዘመን ድረስ ጠብቀው” አለው። 21 ኤርምያስም ለወገኖቹ ሲያለቅስ እያዳፉ አወጡት፤ ከሕዝቡም ጋር እስከ ባቢሎን ድረስ ወሰዱት። 22 ባሮክ ግን አመድ ዘግኖ በራሱ ላይ ነሰነሰ፤ ተቀምጦም አለቀሰ፤ ይህንም ሙሾ አሞሸ። እንዲህም አለ፦ 23 “ስለ ተወደደ ስለ ሕዝቡ ኀጢአት ነው እንጂ ኢየሩሳሌም ስለ ምን ጠፋች? 24 ኃጥኣን እንዳይታበዩ፥ የአምላክንም ከተማ በኀይላችን መያዝ ተቻለን እንዳይሉ በሕዝቡ ኀጢአትና በእኛ ኀጢአት በጠላቶችዋ እጅ ወደቀች እንጂ በእነርሱ ኀይል አይደለም። 25 በእኛ ኀጢአት ለእናንተ ተሰጠቻችሁ እንጂ ይቺን ከተማ መያዝ የተቻላችሁ በእናንተ ጽናት አይደለም። 26 አምላካችንም ያዝንልናል፤ ወደ ሀገራችንም ይመልሰናል፤ ለእናንተ ግን ድኅነት የላችሁም። 27 ከዚህ ዓለም ተለይተው ሄደዋልና፥ የዚችንም ከተማ ጥፋት አላዩምና አባቶቻችን አብርሃምና ይስሐቅ ያዕቆብም ብፁዓን ናቸው።” 28 ይህንም ከተናገረ በኋላ እያለቀሰ ወጣ፤ “ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ስለ አንቺ ኀዘንን አዝናለሁ” አለ። 29 ከከተማውም ወጥቶ በመቃብር ቤት አደረ፤ መላእክትም እየመጡ ሁሉን ይነግሩት ነበር። |