ጦቢት ለእግዚአብሔር ያቀረበው ምስጋና1 ጦቢትም የደስታ መጽሐፍን ጻፈ፤ እንዲህም አለ፥ “ለዘለዓለሙ ሕያው የሚሆን፥ መንግሥቱም ለዘለዓለሙ የሆነ እግዚአብሔር ይመስገን። 2 እርሱ ይገርፋል፤ ይቅርም ይላል፤ እርሱ ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ያወጣልም፤ ከእጁም የሚያመልጥ የለም። 3 እናንተ የእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ እርሱ በመካከላቸው በበተነን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ተገዙለት። 4 በዚያም ገናናነቱን ገለጠላችሁ፤ በሰው ሁሉ ፊትም አክብሩት፤ እርሱ ጌታችን ነውና፥ እርሱ እግዚአብሔር ለዘለዐለም አባታችን ነውና። 5 በኀጢአታችን ይገርፈናል፤ ዳግመኛም ይቅር ይለናል፤ በመካከላቸው ከበተነን ከአሕዛብም ሁሉ ይሰበስበናል። 6 “በፊቱ እውነትን ትሠሩ ዘንድ በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹም ነፍሳችሁም ወደ እርሱ ከተመለሳችሁ ያን ጊዜ እርሱ ወደ እናንተ ይመለሳል። ፊቱንም ከእናንተ አይሰውርም። ከእናንተ ጋር ያደረገውን ታያላችሁ። በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹም ነፍሳችሁም እመኑበት፤ ጻድቅ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ የዘለዓለምን ንጉሥ በተማረካችሁበት ሀገር ከፍ ከፍ አድርጉት፤ እኔም በተማረክሁበት ሀገር አምንበታለሁ፤ ኀጢአተኞች ለሆኑ ለአሕዛብም ኀይሉንና ገናናነቱን እናገራለሁ። እናንተ ኀጢአተኞች፥ ተመልሳችሁ በፊቱ እውነትን ሥሯት፤ ወድዶም ቸርነቱን ለእናንተ ያደርግላችሁ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 7 ፈጣሪዬን ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ሰውነቴም የሰማይን ንጉሥ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። 8 ገናናነቱንም በሁሉ ዘንድ እናገራለሁ። 9 “ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በልጆችሽ ኀጢአት በመከራ አይቀሥፍሽምን? ዳግመኛም ደጋግ ለሆኑ ልጆችሽ ይራራላቸዋል። 10 በበጎ ሥራ ለእግዚአብሔር ተገዢ፤ ባንቺም ዘንድ ድንኳኑ በደስታ እንድትሠራ የዘለዓለሙን ንጉሥ አመስግኚ፤ በዚያም ያሉ የተማረኩ ሰዎች ደስ ይላቸዋል። በዘለዓለማዊ ትውልድም ሁሉ የተጠሉ በአንቺ ምክንያት ይወደዳሉ። 11 “ብዙ አሕዛብ ከሩቅ ወደ ፈጣሪ እግዚአብሔር ስም ይመጣሉ፤ ለሰማይ ንጉሥም እጅ መንሻን ያመጣሉ፥ ትውልድም ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ ለስምህም ምስጋናን ያቀርባሉ። 12 የሚጠሉህ ሁሉ የተረገሙ ናቸው፤ የሚወድዱህ ሁሉ ግን ለዘለዓለሙ የተባረኩ ናቸው። 13 በጻድቃን ልጆች ደስ ይልሃል፤ አቤቱ፥ በአንድነት ተሰብስበው የጻድቃንን ጌታ አንተን ያመሰግናሉና፥ የሚወድዱህ ብፁዓን ናቸውና፤ በሰላምህም ደስ ይላቸዋል። 14 ስለ መከራህ የሚያዝኑ ሁሉ ብፁዓን ናቸው፤ ክብርህን ሁሉ አይተው በአንተ ደስ ይላቸዋልና፤ ለዘለዓለሙም ደስ ይላቸዋል። 15 “ሰውነቴ ገናና ንጉሥ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። 16 ኢየሩሳሌም ሰንፔር በሚባል ዕንቍ ትሠራለችና፥ ግድግዳዋ በመረግድና በከበረ ዕንቍ፥ አዳራሽዋና በሮችዋ በጠራ ወርቅ ይሠራሉና። 17 የኢየሩሳሌም አደባባይም በቢሬሌ፥ በአትራኮስ ዕንቍና በሶፎር ዕንቍ ይሠራልና። 18 በጎዳናዋ ሁሉ ሃሌ ሉያ ይላሉ፤ እያመሰገኑም እንዲህ ይላሉ፥ “እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይመስገን።” |