ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጦቢት የመጨረሻ ምክር 1 ከዚህ በኋላ ጦቢት ከመጸለይ ዝም አለ፤ 2 ዐይኑም በጠፋ ጊዜ አምሳ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበር። ከስምንት ዓመት በኋላም አየ፤ ምጽዋትም መጸወተ፤ ጌታ እግዚአብሔርን መፍራትንም ጨመረ፤ በእርሱም አመነ። 3 ፈጽሞ አረጀ፤ ልጁንና የልጁንም ልጆች ጠራቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “አርጅቻለሁና፥ ለሞትም ደርሻለሁና ልጆችህን አምጣቸው።” 4 ልጄ፥ ወደ ሜዶን ሂድ፤ ትጠፋ ዘንድ እንዳላት ነቢዩ ዮናስ በነነዌ የተናገረውን ነገር ሁሉ አውቃለሁና፤ በሜዶን ግን እስከ ዘመኑ ድረስ ሰላም ይሆናል። ወንድሞቻችንም ከተባረከች ምድር ሁሉ ወደየሀገሩ ይበተኑ ዘንድ አላቸው፤ ኢየሩሳሌምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በእርስዋም ያለ የእግዚአብሔር ቤት ይቃጠላል፤ እስከ ዘመኑም ድረስ ምድረ በዳ ይሆናል። 5 ዳግመኛም እግዝአብሔር ይቅር ብሎ ወደ ሀገራቸው ይመልሳቸዋል፤ ማደሪያው ቤተ መቅደስንም ይሠራሉ፤ የዘመኑ ቍጥር እስከሚፈጸም ነው እንጂ እንደ ቀድሞው አይደለም፤ ከዚህም በኋላ ከተማረኩበት ይመለሳሉ፤ ኢየሩሳሌምንም በክብር ይሠሯታል፤ በእርሷም የእግዚአብሔርን ቤት እስከ ልጅ ልጅ ዘመን ድረስ በዕብነ በረድ ይሠራሉ። 6 አሕዛብም ሁሉ በእውነት ወደ እርሱ ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔርንም ይፈሩታል፤ ጣዖቶቻቸውንም ይጥላሉ። 7 አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ሕዝቡም በእርሱ ያምናሉ፤ እግዚአብሔርም ወገኖቹን ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል። በእውነትና በቅንነት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ሁሉ ደስ ይላቸዋል፤ ለወንድሞቻቸውም ቸርነትን ያደርጋሉ። 8 “ልጄ ሆይ! አሁንም ከነነዌ ውጣ፤ ነቢዩ ዮናስ የተናገረው ነገር በግድ ይደረጋልና። 9 አንተ ግን ትእዛዙንና ሕጉን ጠብቅ፤ ይቅር ባይም ሁን፤ በጎ ይደረግልህ ዘንድ እውነትን ውደድ። 10 አክብረህ ቅበረኝ፤ እናትህንም ከእኔ ጋር ቅበራት። ልጄ፥ በነነዌ አትቈይ። ሐማ በዘመድህ በአኪአክሮስ ያደረገውን፥ ከብርሃን ወደ ጨለማ እንዳገባው፥ ፍዳውንም እንደ ተቀበለ፥ አኪአክሮስም እንደ ዳነ እይ። እርሱ ግን ፍዳውን ተቀበለ፤ እርሱ ወደ ጨለማ ወረደ። ምናሴ ምጽዋትን አደረገ፤ እውነትንም አደረገ፤ ከመከሩበት ከሞት መቅሠፍትም ዳነ። ሐማ ግን በዚያች ወጥመድ ወደቀና ሞተ። የጦቢትና የሚስቱ ሞት 11 “አሁንም ልጄ፥ ምጽዋት የምታደርገውን እይ፤ ከሞት ታድናለች፤ ታጸድቃለችም።” ጦቢትም ይህን ተናግሮ ሞተ፤ ባልጋው ላይ ሳለም ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። መቶ አምሳ ስምንት ዐመትም ሆኖት ነበር። በክብርም ቀበሩት፤ 12 እናቱ ሐናም በሞተች ጊዜ ካባቱ ጋራ ቀበራት። ጦብያም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር አማቱ ራጉኤል ወዳለበት ወደ ባጥና ሄደ። 13 ራጉኤልና ሚስቱ አድናም አርጅተው ሞቱ። አማቶቹንም አክብሮ ቀበራቸው። ገንዘባቸውንም ሁሉ ወረሰ። የአባቱን የጦቢትን ገንዘብም ወረሰ። 14 ጦብያም በመቶ ሃያ ሰባት ዓመቱ ሞተ፤ የሜዶን ክፍል በምትሆን በባጥናም ተቀበረ። 15 አባቱም እንደ ነገረው ሳይሞት የነነዌን ጥፋት ሰማ። ናቡከደነፆርና አሕሻዊሮስም የነነዌን ጥፋት ሰምተው ደስ አላቸው። የጦቢትና የልጁ የጦብያ ነገር ተፈጸመ። ለእግዚአብሔር ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው አሜን። |