Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽ​ሐፈ ጦቢት 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ለሩ​ፋ​ኤል የታ​ሰበ የአ​ገ​ል​ግ​ሎት ዋጋ

1 ከዚ​ህም በኋላ ጦቢት ጦብ​ያን ጠርቶ፥“ ልጄ ሆይ፥ ከአ​ንተ ጋራ የሄደ የዚ​ህን ሰው ደመ​ወ​ዙን እይ​ለት፤ ዳግ​መ​ኛም ትጨ​ም​ር​ለት ዘንድ ይገ​ባል” አለው።

2 ጦብ​ያም አባ​ቱን እን​ዲህ አለው፥ “ያመ​ጣ​ሁ​ትን የገ​ን​ዘ​ቤን እኩ​ሌታ ስንኳ ብሰ​ጠው የሚ​ጐ​ዳኝ የለም።

3 ወደ አንተ በደ​ኅና መል​ሶ​ኛ​ልና፥ ሚስ​ቴ​ንም ፈው​ሷ​ታ​ልና፤ ብሩ​ንም አም​ጥ​ቶ​ል​ኛ​ልና፤ እን​ዲ​ሁም አን​ተን ፈው​ሶ​ሃ​ልና።”

4 አባ​ቱም፥ “እው​ነት ተና​ገ​ርህ” አለው።

5 ያንም መል​አክ ጠርቶ እን​ዲህ አለው፥ “ከእ​ና​ንተ ጋር ካመ​ጣ​ች​ሁት ሁሉ እኩ​ሌ​ታ​ውን ይዘህ በደ​ኅና ሂድ።”

6 ሩፋ​ኤ​ልም ያን​ጊዜ ሁለ​ቱን ሁሉ ጠራ​ቸው፤ ገለል አድ​ር​ጎም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አመ​ስ​ግ​ኑት፤ ለእ​ር​ሱም ተገዙ፤ ለስ​ሙም ምስ​ጋና አቅ​ርቡ፤ ስላ​ደ​ረ​ገ​ላ​ች​ሁም በጎ ነገር ሁሉ በሰው ሁሉ ፊት እመ​ኑ​በት፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አመ​ስ​ግ​ኑት፤ ስሙ​ንም አመ​ስ​ግኑ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ሥራ በክ​ብር ተና​ገሩ፤ ተአ​ም​ራ​ቱ​ንም ግለጡ፤ እር​ሱ​ንም ከማ​መ​ስ​ገን ቸል አት​በሉ።

7 የመ​ን​ግ​ሥ​ትን ምሥ​ጢር ሊሰ​ው​ሩት፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሥራ ግን በክ​ብር ሊገ​ል​ጡት ይገ​ባ​ልና፤ መከ​ራም እን​ዳ​ታ​ገ​ኛ​ችሁ በጎ ሥራን ሥሯት።

8 ጸሎት ከጾም፥ ከም​ጽ​ዋ​ትና ከጽ​ድቅ ጋር መል​ካም ነው። ከብዙ የዓ​መፅ ገን​ዘብ ጥቂት የእ​ው​ነት ገን​ዘብ ይሻ​ላል፤ ወር​ቅ​ንም ከማ​ድ​ለብ ምጽ​ዋት መስ​ጠት ይሻ​ላል።

9 ምጽ​ዋት ከሞት ታድ​ና​ለች፤ ከኀ​ጢ​አ​ትም ሁሉ ታነ​ጻ​ለ​ችና፥ ጽድ​ቅ​ንና ምጽ​ዋ​ትን የሚ​ያ​ደ​ር​ጉም ሁሉ ለራ​ሳ​ቸው ሕይ​ወ​ትን ይሞ​ላሉ።

10 የሚ​በ​ድሉ ግን ሕይ​ወ​ታ​ቸ​ውን ይጠ​ሏ​ታል።

11 “እነሆ፥ ነገ​ሩን ሁሉ ከእ​ና​ንተ አል​ሰ​ው​ርም፤ የመ​ን​ግ​ሥ​ትን ምሥ​ጢር ሊሰ​ው​ሩት የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሥራ ግን በክ​ብር ሊገ​ል​ጡት መል​ካም እንደ ሆነ እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ።

12 እነሆ፥ አን​ተና ምራ​ትህ ሣራ በጸ​ለ​ያ​ችሁ ጊዜ የል​መ​ና​ች​ሁን መታ​ሰ​ቢያ እኔ በቅ​ዱሱ ፊት አቀ​ረ​ብሁ፤ አን​ተም ሬሳ በቀ​በ​ርህ ጊዜ ያን​ጊዜ እኔ ካንተ ጋራ ነበ​ርሁ።

13 ቸል ባላ​ልህ ጊዜ፥ ምሳ​ህ​ንም ትተህ በተ​ነ​ሣህ ጊዜ፥ ሬሳ​ንም ትቀ​ብር ዘንድ በሄ​ድህ ጊዜ፥ በጎ ሥራን መሥ​ራ​ት​ንም ባል​ዘ​ነ​ጋህ ጊዜ እኔ ከአ​ንተ ጋር ነበ​ርሁ።

14 አሁ​ንም፦ ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አን​ተን አድ​ንህ ዘንድ፥ ምራ​ትህ ሣራ​ንም ከኀ​ዘኗ አረ​ጋ​ጋት ዘንድ ላከኝ።

15 የቅ​ዱ​ሳ​ንን ጸሎት ከሚ​ያ​ሳ​ርጉ፥ በገ​ና​ና​ውና በቅ​ዱሱ ጌት​ነት ፊት ከሚ​ያ​ቀ​ርቡ ሰባቱ ቅዱ​ሳን መላ​እ​ክት አንዱ መል​አክ እኔ ሩፋ​ኤል ነኝ” አላ​ቸው።

16 ይህ​ንም ሰም​ተው ሁለቱ ደነ​ገጡ፤ ፈር​ተ​ዋ​ል​ምና በግ​ም​ባ​ራ​ቸው ወደቁ።

17 መል​አ​ኩም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “አት​ፍሩ፤ ነገር ግን አም​ላ​ካ​ችሁ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፍሩት፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ፈጽ​ማ​ችሁ አመ​ስ​ግ​ኑት፤

18 ምስ​ጋና ለእኔ አይ​ገ​ባ​ኝ​ምና፥ ነገር ግን የአ​ም​ላ​ካ​ችሁ ፈቃድ አመ​ጣኝ፤ ስለ​ዚ​ህም በዘ​መ​ናት ሁሉ ለዘ​ለ​ዓ​ለሙ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አመ​ስ​ግ​ኑት።

19 እኔም ተገ​ለ​ጥ​ሁ​ላ​ችሁ፤ ነገር ግን እይ​ታን አያ​ችሁ እንጂ ከእ​ና​ንተ ጋር አል​በ​ላ​ሁም፤ አል​ጠ​ጣ​ሁ​ምም።

20 አሁ​ንም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እመኑ፥ ወደ ላከ​ኝም ወደ ላይ እወ​ጣ​ለ​ሁና ይህን ሁሉ በመ​ጽ​ሐፍ ጻፉት” አለ።

21 ያን ጊዜም ተነ​ሥቶ ሄደ፤ ከዚያ በኋ​ላም አላ​ዩ​ትም።

22 የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ስለ ተገ​ለ​ጸ​ላ​ቸው፥ ገና​ናና ድንቅ በሚ​ሆን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥራ ሁሉ አመኑ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች