Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ግብፃውያን በኤርትራ ባሕር እንደ ሰጠሙ 1 በዝንጉዎች ላይ ግን ያለ ርኅራኄ ፈጽማ እስክትጨርሳቸው ድረስ መዓትህ ጸናች። የሚደረግ ሥራቸውን አስቀድመው ዐውቀዋልና። 2 እነዚያ ከመሄድ መልሰዋቸዋልና፥ ዳግመኛም በብዙ ችኮላ ሰድደዋቸዋልና፥ በተጸጸቱም ጊዜ በሩጫ ገሠገሡ፥ በፊታቸውም ማዕበል አለ ብለው ተከተሏቸው። 3 ገና በልቅሶ ሳሉ፥ በመቃብሮቻቸውም ላይ ሲጮኹ ልዩ የስንፍና ዐሳብ ስቧቸዋልና፥ ከእነርሱ ይሄዱ ዘንድ ማልደው ያስወጧቸውን እንደ ኰበለሉ ሰዎች ይከተሏቸው ዘንድ በሩጫ ገሠገሡ። 4 የተገቧት የመከራ መጨረሻ ወደዚህ ሥራ ሳበቻቸው፤ ዝንጋዔም አሳታቸው፥ የጐደለውንም ፍርድ በፍርዶች ቍጥር ይፈጽሙና ይሞሉ ዘንድ ያገኛቸውን መከራ አላሰቡም። 5 ወገኖችህ ግን ድንቅ መንገድን ሄዱ፥ እነዚያም ክፉ ሞትን አገኙ። እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ጠበቃቸውና እንደ አዳናቸው 6 ፍጥረት ሁላ ከወገኖችዋ ጋር በእነርሱ ላይ ተለወጠች፤ ዳግመኛ ልጆችህ ያለ ክፋት በደኅና ይጠበቁባት ዘንድ የታዘዘችበትን ትእዛዝ እያገለገለች ተለወጠች። 7 ደመና ሰፈሩን ጋረደች፥ ውኃዋም ከቀድሞዋ ይልቅ የረጋች ሆና ታየች፥ የደረቀችውም ምድር የለመለመች መስክ ሆና ታየች፥ በኤርትራ ባሕር መካከልም መሰናክል የሌለው መንገድ ታየ። 8 በከበረች እጅህና ከፍ ባለች ክንድህ ተጋርደው፥ ወገኖችህ ሁሉ ባለፉበት ኀይለኛ ማዕበል መካከልም የለመለመ መስክ ታየ፤ ድንቅ ሥራህንም ባዩ ጊዜ ይህችን እጅህን አመሰገኑ። 9 አቤቱ፥ ያዳንሃቸው እነርሱ አንተን እያመሰገኑ እንደ ፈረሶች ተሰማሩ፥ እንደ ወይፈኖችም ዘለሉ። 10 በባዕድ ሀገር በእንግድነት በነበሩ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ዐስበዋልና፤ ምድራቸው እንስሳትን በማስገኘት ፋንታ ተቈናጣጭ ዝንብን እንዴት አወጣች? ባሕርስ በብዙው ውኃ ውስጥ በነበረው ዓሣ ፋንታ ጓጕንቸርን እንዴት አስገኘች? 11 ከዚህም በኋላ መናውን በመገብሃቸው ጊዜ፥ አዲስ የአዕዋፍ ፍጥረትን አዩ፥ የተድላና የደስታ ምግብን በተመኙና በለመኑ ጊዜም፥ ብዙ ፍላጎታቸውን ለማርካት ከባሕር ውስጥ ብዙ ድርጭት ወጣላቸው። 12 ከመብረቆች ያልራቀች ቀድሞ በተአምር በተደረገው የመቅሠፍት ኀይል የምትመሰል መቅሠፍት በኃጥኣን ላይ መጣች፥ እነርሱ እንደ ክፋታቸው ሚዛን በእውነት ተፈርዶባቸዋልና። 13 እንግዶችን ስለ መቀበል እጅግ የተጠላ ጠባይን ወድደዋልና፥ እነዚህ የማያውቋቸው በደረሱ ጊዜ አልተቀበሉአቸውም፤ እነዚያ ግን መልካም እያደረጉ ሲጠቅሙአቸው በእነርሱ ዘንድ በእንግድነት የኖሩትን አስጨንቀው ገዙአቸው። 14 በዚህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለሥራቸው መጐብኛና መመርመሪያ ይሆን ዘንድ ነው፥ በእነርሱ ዘንድ እንግዳ የሆኑትን በጭንቅ ይቀበሏቸው ነበርና። 15 እነዚህ ግን በዓል በማድረግ የተቀበሏቸውንና ከእነርሱ የአንድ ሕግ ተካፋዮች ያደረጓቸውን ጻድቃን በጭንቅ መከራ አጸኑባቸው። 16 ስለዚህ በጻድቃን ደጃፍ እንደ ተሰበሰቡ እንደ እነዚያ ሰዎች ብርሃንን በማጣት ተቀጡ፥ ድንገት በጥልቅ ጨለማ ተግዘዋልና፥ ከእነርሱም እያንዳንዱ የቤቱን የደጃፉን መግቢያ መንገድ ይፈልግ ነበር። 17 ብርሃናት ከባሕርያቸው ተለውጠውባቸው ነበርና፤ የዜማውን ነገር በማወቅ የበገናው ስም እንደሚለወጥ፥ የቀናም ሆኖ በዜማው ጸንቶ እንደሚኖር በየወገናቸው የተፈጠሩትን በማየት ፈጽሞ የሚሰፈር ሥራም፥ እንዲሁ ነው። የእግዚአብሔር ተአምራዊ ኀይል 18 በደረቅ ያሉ ፍጥረቶች ወደ ውኃ ተመልሰዋልና፥ በውኃ የሚንቀሳቀሱና የሚዋኙ ፍጥረታትም ኑሮአቸው ወደ የብስተመልሷልና። 19 እሳቱም በውኃው ውስጥ ፈጽሞ በረታ፥ ውኃውም የባሕርዩን ተፈጥሮ ሰወረ። 20 ፈጥኖ የሚጠፋ የእሳቱም ነበልባል ሥራው ባይደለ በመካከላቸው ወዲያና ወዲህ እያለና እየተመላለሰ የከብቶችን ሥጋ አላቃጠለም። የማይጠፋ የፍጥረታት ወገን እሳትም ፈጥኖ የሚቀልጥ ውርጭን አላቀለጠውም። አቤቱ፥ በሥራው ሁሉ የወገኖችህን ክብር ፈጽመህ አብዝተሃልና። በሁሉም አክብረሃቸዋልና ወደ እኛም በመጣው ነገር ሁሉ ቸርነትህን አላራቅህብንም፥ እኛንም በየጊዜው ቸል አላልኸንም፥ በየቦታውም ሁሉ በዚያ አንተ ትኖራለህ። |