Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እውነተኛውን አምላክ የማምለክ ጥቅም 1 አንተ ፈጣሪያችን ግን ቸር፥ እውነተኛ፥ ታጋሽም ነህ፥ በምሕረትህም ሁሉን ትሠራለህ። 2 ኀይልህን እያወቅን ብንበድል፥ ያንተ መሆናችንን እያወቅንም ባንበድል ያንተ ነን። 3 አንተን ማወቅ ፍጽምት ጽድቅ ናትና፥ ኀይልህንም ማወቅ የሕይወት ሥር ናትና። 4 ክፉ ዐሳብ፥ የሰው ጥበብ፥ ፍሬ የሌለው የማስጌጥ ድካም፥ ወይም ቀለም በመቀባት መልካቸው የሚለወጥ ሥራዎች አያስቱንምና። 5 የእነዚህም መልካቸው እነርሱን ወደ መመኘት ይመጣ ዘንድ አላዋቂን ሰው ይስበዋል፤ ነፍስና መንቀሳቀስ የሌለው ምውት ጣዖትንም ያስወድደዋል። 6 የሚሠሯቸው የሚወዷቸውና የሚያመልኳቸውም ክፋትን የሚወድዱ ናቸው። እንደዚህም የሚያደርጉ በእነርሱ ላይ ተስፋ ያደርጋሉ። የሸክላ ጣዖትን የማምለክ ሞኝነት 7 ሸክላ ሠሪ ለስላሳ አፈርን በለወሰ ጊዜ ከእኛ ለእያንዳንዱ ሁሉ ሊያገለግል የሚገባውን የተለያየ ሥራን ይሠራል፥ ነገር ግን ከዚያው ጭቃ ለንጹሕ ሥራ አገልግሎት ዕቃዎችን ይሠራል፥ እንደዚሁም ለሌሎች ሥራዎች በእነዚህ አምሳል ይሠራል፤ የእነዚህም ሁሉ ተግባር ለተለያየ መፍቅድ ነው፥ ነገር ግን ይህ ወይም ያ ለምን ጥቅም እንደሚውል ፈራጁ ዳኛ ሸክላ ሠሪው ነው። 8 ለክፋት የሚደክም ሰው ግን ከዚያ ጭቃ ከንቱ ጣዖትን ይሠራል፥ ይህም ከጥቂት ቀን አስቀድሞ ከምድር ተሠራ፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ ከእርሷ ወደ ወጣባት ምድር ይመለስ ዘንድ አለው፥ ስለ ነፍሱ ፍርድም ይመረመራል። 9 በእርሱም ዘንድ ያለው ትጋት ይሠራና ይደክም ዘንድ ስላለውና ሕይወቱም ጥቂት ስለሆነ አይደለም። ወርቅና ብርን የሚሠሩ ሰዎችን ይፎካከራቸው ዘንድ ነው እንጂ፤ ናስ ሠሪዎችንም ይመስላቸው ዘንድ ነው እንጂ፥ የተዋረደውንም ሠርቶ ክብር ይሰጠዋል። 10 ልቡናው አመድ ነው፥ ተስፋውም ከአፈር ይጐሰቍላል፥ ሕይወቱም ከጭቃ እጅግ የተናቀ ነው። 11 የፈጠረውንና ነባቢት ነፍስን ያሳደረበትን፥ የሕይወት መንፈስንም እፍ ያለበትን አላወቀውምና። 12 ነገር ግን እነዚህ ሕይወታችንን ጨዋታና መዘባበቻ አድርገው ዐሰቡ፥ ኑሯችንንም የትርፍ ምልክት አደረጉት፤ ስላጣሁ ይጨንቀኛል ብሏልና፥ ከዚህም በኋላ ያተርፋል፥ ክፋትንም ገንዘብ ያደርጋል። 13 ይህም ከሁሉ ፈጽሞ እንደሚበድል ታወቀ፥ በምድር ከሚታየውና ፈጥኖ ከሚጠፋው ከእንጨት የተቀረፀ ጣዖትን ሠርትዋልና። 14 ሁሉም አላዋቂዎችና ጐስቋሎች ናቸው፥ ሁሉም ከተማረኩ ወገኖች ተለይተው ሙታን ናቸው፥ በእርሱ የታሰሩም ሰዎች ከሕፃናት ሰውነት ይልቅ ስንፍናን ያበዛሉ። 15 መሥራት የማይቻላቸው፥ በዐይናቸው ማየት፥ ባፍንጫቸው ነፋስን ማሽተት፥ በጆሮአቸውም መስማት፥ በእጆቻቸው ጣቶች መዳሰስ የማይቻላቸው፥ እግሮቻቸውም ከመሄድ የቦዘኑ የአሕዛብን ጣዖቶች አማልክት አድርገው ዐስበዋልና። 16 ሰው ሠርትዋቸዋልና፥ መንፈስ የተከፈለውም ሰው ቀርፆአቸዋልና፥ ራሱን አስመስሎ አምላክን ይሠራ ዘንድ ለሰው አይቻለውምና። 17 እርሱ መዋቲ ሲሆን በኀጢአት እጅ መዋቲን ይሠራል፥ እርሱ ሕያው ስለሆነ እነዚህ ግን ከቶ ሕያዋን ስላይደሉ ከጣዖቶቹ ይሻላልና። 18 እንስሳዎችንም አማልክት ያደረጓቸው እነዚህ በስንፍና ያመልኳቸዋል፥ እነዚህን ግን በሕሊና ቢመዝኗቸው ከሌሎች አማልክት ይከፋሉ። 19 ምኞትን የወደደም እንስሳትን በማየት ከእነርሱ በአንዱ ምኞቱን ፈጸመ፥ በአንዱም በደለ፥ የእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር በዚህ ርቋልና። |