ዘሌዋውያን 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሃይማኖት በዓላት 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ቅዱሳት ጉባኤያት ብላችሁ የምትጠሩአቸው በዓላቴ፥ የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 3 ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። 4 እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሱ ጉባኤያት ናቸው። በዓለ ፋሲካና በዓለ ናዕት ( ዘኍ. 28፥16-25 ) 5 “በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚእብሔር ፋሲካ ነው። 6 በዚህም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ ብሉ። 7 መጀመሪያይቱ ቀን ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩባት። 8 ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ሰባተኛዋ ቀን ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩባት።” 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ መከሩንም ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ 11 እርሱም ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ያቀርበዋል፤ በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ካህኑ ያቅርበው፤ 12 ነዶውንም ባቀረባችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 13 የስንዴም ቍርባን ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም የስንዴ ዱቄት ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው ቍርባን ይሁን፤ የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን። 14 እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት የአምላካችሁን ቍርባን እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው። በዓለ ሠዊት ( ዘኍ. 28፥26-31 ) 15 “ያቀረባችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ሱባዔ ቍጠሩ፤ 16 እስከ መጨረሻዋ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 17 ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም የስንዴ ዱቄት የተሠራ ሁለት የቍርባን እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ከእህላችሁ ቀዳምያት ለእግዚአብሔር በእርሾ ይጋገራል። 18 ከኅብስቱም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ ከመንጋውም አንድ ወይፈን፥ ሁለትም ነውር የሌለባቸው አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው መሥዋዕት እንዲሆን መሥዋዕታቸውና ቍርባናቸው፥ ወይናቸውም ለእግዚአብሔር ይሁን። 19 አንድም አውራ ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ከመጀመሪያው የእህል ቍርባን ጋር ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። 20 ካህኑም ከበኵራቱ ኅብስት፥ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለቍርባን ያቅርበው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ላቀረበው ለካህኑ ይሁን። 21 ያችንም ቀን ቅድስት ጉባኤ ብላችሁ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ነው። 22 “የምድራችሁን መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ በእርሻችሁ የቀረውን አጥርታችሁ አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።” በዓለ መጥቅዕ ( ዘኍ. 29፥1-6 ) 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በሰባተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰች ጉባኤ ትሁንላችሁ። 25 የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ።” ዕለተ አስተስርዮ ( ዘኍ. 29፥7-11 ) 26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 27 “በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛዋ ቀን የማስተስረያ ቀን ናት፤ ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቋት፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። 28 በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እናንተ ማስተስረያ ትሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ናትና በዚያች ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩባት። 29 በዚያችም ቀን ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 30 በዚያችም ቀን ሥራ የሚሠራ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። 31 ሥራ ሁሉ አታድርጉባት፤ በምትቀመጡበት ሀገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሕግ ነው። 32 የዕረፍት ሰንበት ትሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን ከማታ ጀምራችሁ እስከ ዐሥረኛው ቀን ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ።” የዳስ በዓል ( ዘኍ. 29፥12-40 ) 33 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 34 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። 35 የመጀመሪያዋ ቀን ቅድስት ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉባት። 36 ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ስምንተኛዋም ቀን የተቀደሰች ጉባኤ ትሁንላችሁ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቡ፤ የመሰናበቻ በዓል ነውና፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 37 “የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ በዓላት እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38 እነዚህም ከእግዚአብሔር ሰንበታት ሌላ፥ ለእግዚአብሔርም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለቶቻችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው። 39 ከሰባተኛውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ታደርጋላችሁ፤ የመጀመሪያዋ ቀን ዕረፍት ትሁን፤ ስምንተኛዋም ቀን ዕረፍት ትሁን። 40 በመጀመሪያዋ ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባውንም ቅርንጫፍ፥ የለመለመውንም ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት በየዓመቱ ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። 41 በየዓመቱ በሰባተኛው ወር ይህን በዓል ታደርጉ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሕግ ይሁንላችሁ። 42 ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ 43 ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የሀገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።” 44 ሙሴም የጌታን የእግዚአብሔርን በዓላት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ተናገረ። |