ዘሌዋውያን 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የመሥዋዕት ቅድስና 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ፥ የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3 እንዲህ በላቸው፦ ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ በትውልዳችሁ ርኵሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱስ ነገር ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 4 ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ። ከበድንም የተነሣ ርኩስ የሆነውን፥ ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስስበትን የሚነካ፥ 5 ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ፥ ወይም በሁሉ ዐይነት የረከሰውን ሰው የሚነካ፥ 6 እነዚህን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ። 7 ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ምግቡ ነውና ከተቀደሰው ይብላ። 8 በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን፥ አውሬም የሰበረውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 9 ቢያረክሱአት እንዳይሞቱ፥ ስለ እርስዋም ኀጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ሕግን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 10 “ከባዕድ ወገን የሆነ ሰው ከተቀደሰው አይብላ፤ የካህኑም እንግዳ፥ ደመወዘኛውም ከተቀደሰው አይብላ። 11 ካህኑ ግን በገንዘቡ አገልጋይ ቢገዛ እርሱ ከምግቡ ይብላ፤ በቤቱም የተወለዱት ከእንጀራው ይብሉ። 12 የካህንም ልጅ ከሌላ ወገን ጋር ብትጋባ፥ እርስዋ ከተቀደሰው ዐሥራት አትብላ። 13 የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነቷ እንደ ነበረች ወደ አባቷ ቤት ብትመለስ፥ ከአባቷ እንጀራ ትብላ፤ ከሌላ ወገን የሆነ ባዕድ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ። 14 ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ቢበላ አምስተኛ እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ለካህኑ ይስጥ። 15 ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡትን፥ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የተቀደሰውን ነገር አያርክሱ። 16 በኀጢአት ሳሉ ከተቀደሰው መሥዋዕት ከበሉ ግን ኀጢአትና በደል ይሆንባቸዋል፤ የማነጻቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” 17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 18 “ለአሮንና ለልጆቹ፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጡት እንግዶች ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቍርባን ቢያቀርብ፥ 19 ይሠምርላችሁ ዘንድ ከበሬ፥ ወይም ከበግ፥ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ። 20 ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ነውር ያለበትን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ። 21 ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን፥ ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሰምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፤ ነውርም አይሁንበት። 22 ዕውር፥ ወይም ሰባራ፥ ወይም ምላሱ የተቈረጠ፥ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበት፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህንም ለእሳት ቍርባን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአሔር አታሳርጉ። 23 በሬው፥ ወይም በጉ ጆሮው፥ ወይም ጅራቱ የተቈረጠ ቢሆን፥ ቈጥረህ የራስህ ገንዘብ አድርገው እንጂ ለስእለት አይቀበልህም። 24 የተቀጠቀጠውን፥ ወይም የተሰበረውን፥ ወይም የተቈረጠውን ወይም የተሰነጋውን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ። 25 ከእነዚህም ከባዕድ ወገን ከሆነ ሰው እጅ ለአምላካችሁ መባ አታቅርቡ፤ ርኵሰትም፥ ነውርም አለባቸውና አይቀበላችሁም።” 26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 27 “ላም፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን፥ ከዚያም በላይ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን የሠመረ ይሆናል። 28 ላም፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ብትሆን እርስዋንና ልጅዋን በአንድ ቀን አትረዱ። 29 የምስጋናንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሠዉ እንዲቀበላችሁ ሠዉለት። 30 በዚያው ቀን ይብሉት፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 31 ትእዛዛቴን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 32 የተቀደሰውንም ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤ 33 የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። አምላካችሁም እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” |