ዕዝራ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከባዕዳን ወገን የተጋቡ የእስራኤል ሰዎች እንዲፋቱ ስለ ማድረግ 1 ዕዝራም እያለቀሰና በእግዚአብሔር ፊት እየወደቀ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ የወንድና የሴት፥ የሕፃናትም እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። 2 ከኤላም ልጆች ወገን የነበረውም የኢያሔል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “አምላካችንን በድለናል፤ የምድርንም አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፤ አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ። 3 አሁንም እንደ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩት ምክር፥ ሴቶችን ሁሉ፥ ከእነርሱም የተወለዱትን እንሰድድ ዘንድ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ። ተነሥ እንደ አምላካችንም ትእዛዝ ገሥፃቸው፤ እንደ ሕጉም ያድርጉ፤ 4 ይህም ነገር ለአንተ ይገባልና፥ እኛም ከአንተ ጋር ነንና ተነሣ፤ በርታ፤ አድርገውም።” 5 ዕዝራም ተነሣ፤ አለቆቹንና ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም፥ እስራኤልን ሁሉ እንደዚህ ቃል ያደርጉ ዘንድ አማላቸው፤ እነርሱም ማሉ። 6 ዕዝራም ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤሊያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ጓዳ ገባ፤ ስለ ምርኮኞቹም ኀጢአት ያለቅስ ነበርና ገብቶ እንጀራ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም። 7 የምርኮ ልጆች ሁሉም ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ዘንድ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ዐዋጅ ነገረ 8 “እስከ ሦስት ቀን ድረስ የማይመጣ ሁሉ እንደ ሽማግሎችና እንዳለቆች ምክር ከብቱ ሁሉ ይበዝበዝ፤ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ ይለይ” ብሎ ዐዋጅ አስነገረ። 9 ሦስት ቀንም ሳያልፍ በዘጠነኛው ወር ከወሩም በሃያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። 10 ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ፥ “ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። 11 አሁንም የአባቶቻችንን አምላክ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ” አላቸው። 12 ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ መልሰው እንዲህ አሉ፥ “እንደ ተናገርኸን እናደርግ ዘንድ ይገባናል። 13 ነገር ግን የሕዝቡ ቍጥር ብዙ ነው፤ ጊዜውም የትልቅ ዝናብ ጊዜ ነው፤ በሜዳም ልንቆም አንችልም፤ በዚህም ነገር እጅግ በድለናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። 14 አለቆቻችንም በጉባኤው ፋንታ ሁሉ ይቁሙ፤ ስለዚህም ነገር የአምላካችን ጽኑ ቍጣ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት በከተሞቻችን ያሉት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፤ ከእነርሱም ጋር የከተማው ሁሉ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ።” 15 ነገር ግን የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሐዝያ ስለዚህ ነገር ከእኔ ጋር ናቸው፤ ሜሱላምና ሌዋዊው ሰባታይም ይረዱአቸው ነበር። 16 የስደተኞቹም ልጆች እንዲህ አደረጉ፤ ካህኑ ዕዝራ፥ የአባቶችም ቤቶች አለቆች በየአባቶቻቸው ቤቶች ሁሉም በየስማቸው ተለዩ፤ በዐሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ይመረምሩ ዘንድ ተቀመጡ። 17 እስከ መጀመሪያውም ወር እስከ መጀመሪያው ቀን ድረስ ሠርተው እንግዶቹን ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ። ከአሕዛብ ሴቶች ሚስትን ያገቡ የእስራኤል ልጆች 18 ከካህናቱም ወገን ልጆች እንግዶቹን ሴቶች ያገቡ ሰዎች ተገኙ፤ ከኢዮሴዴቅ ልጅ ከኢያሱ ልጆችና ከወንድሞቹ ማዓሥያ፥ አልዓዛር፥ ኦሬም፥ ገዳልያ። 19 ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ዘንድ እጃቸውን ሰጡ፤ ስለ በደላቸውም ከመንጋው አንድ አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት አቀረቡ። 20 ከኢሚር ልጆችም አናኒና ዝብድያ። 21 ከኤራም ልጆችም መሳሔል፥ ኤልያ፥ ሴሚያ፥ ያሔል፥ ዖዝያ። 22 ከጳሰኮር ልጆችም ኤልዮና፥ መሐሰዓ፥ ይስማኤል፥ ናትናኤል፥ ኢዮዛባድ፥ ኤልሣ። 23 ከሌዋውያንም ኢዮዛባድ፥ ሰሜኢ፥ ቆሊጣስ የሚባል ቆልያ፥ ፈዲሓ፥ ይሁዳ፥ አልዓዛር። 24 ከመዘምራንም ኤልያሴብ፤ ከበረኞችም ሰሎም፥ ጤሎም፥ ኡሪ። 25 ከእስራኤልም ከፋሮስ ልጆች ራምያ፥ ዖዝያ፥ መልክያ፥ ሚያሚን፥ አልዓዛር፥ መልክያ፥ ቤንያህ። 26 ከኤላም ልጆችም መታንያ፥ ዘካርያስ፥ ኢያኤል፥ አብዲ፥ ይሬሞት፥ ኤልያ። 27 ከዛቱ ልጆችም ዔሊዔናይ፥ ኤልያሴብ፥ መታንያ፥ ኤርሞት፥ ዛባድ፥ ዓዚዛ። 28 ከቤባይ ልጆችም ዮሐናን፥ ሐናንያ፥ ዘባይ፥ አጥላይ። 29 ከባኒ ልጆችም ሜሱላም፥ መሉክ፥ ዓዳያ፥ ያሱብ፥ ሳዓል፥ ራሞት። 30 ከፈሐት ሞዓብ ልጆችም ዓድና፥ ክላል፥ በናያስ፥ ማዕሴያ፥ መታንያ፥ ባስልኤል፥ በነዊ፥ ምናሴ። 31 ከኤራም ልጆችም አልዓዛር፥ ይሲያ፥ ሚልክያ፥ ሰማያ፥ ስምዖን፥ 32 ብንያም፥ መሉክ፥ ሰማርያ። 33 ከሐሱም ልጆችም መታንያ፥ መታታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፋልጥ፥ ይሬማይ፥ ምናሴ፥ ሰሜኢ። 34 ከባኒ ልጆችም ማዕዳይ፥ ዓምራም፥ ኡኤል፥ 35 በናያስ፥ በዳያ፥ ኬልቅያ፥ 36 ውንያ፥ መሪሙት፥ ኤልያሴብ፤ 37 መታንያ፥ መትናይ፥ የዕሡ፤ 38 የባኔይ ልጆችና የሰሜይ ልጆች፤ 39 ሰሌምያ፥ ናታን፥ ሐዳያ፤ 40 መክነድባይ፥ ሴሴይ፥ ሰራይ፤ 41 ኤዛርኤል፥ ሰሌምያ፥ ሰማርያ፥ 42 ሰሎም፥ አማርያ፥ ዮሴፍ። 43 ከናቡ ልጆችም ይዒኤል፥ መታትያ፥ ዛባድ፥ ዛብንያ፥ ያዳይ፥ ኢዮኤል፥ በናያስ። 44 እነዚህ ሁሉ እንግዶቹን ሚስቶች አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም ሚስቶች ዐያሌዎቹ ልጆችን ወልደው ነበር። |