መክብብ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እኔ በልቤ፥ “ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ እነሆ፥ መልካምንም እይ” አልሁ፤ ይህም እነሆ፥ ከንቱ ነበረ። 2 ሣቅን፥ “ሽንገላ ነህ፤ ደስታንም፦ ምን ታደርጋለህ?” አልሁት። 3 የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች የሚሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ደስ ለማሰኘት፥ ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። 4 እኔ ሥራዬን አበዛሁ፥ ቤቶችንም ለእኔ ሠራሁ፥ ወይንም ተከልሁ። 5 የወይንና የአትክልት ቦታን አደረግሁ፥ ወይንና ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው። 6 የሚያፈራ እንጨትንና የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያን አደረግሁ። 7 ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ገዛሁ፤ በቤት የተወለዱ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ የበጎችና የከብቶች መንጋዎች ነበሩኝ። 8 ብርንና ወርቅን፥ የከበረውንም የነገሥታትንና የአውራጆችን መዝገብ ለራሴ ሰበሰብሁ፤ ሴቶችና ወንዶች አዝማሪዎችን፥ የሰዎች ልጆችንም ተድላ አደረግሁ፤ የወይን ጠጅ ጠማቂዎችንና አሳላፊዎችንም አበዛሁ። 9 ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ታላቅም ሆንሁ። ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸናችልኝ። 10 ዐይኖቼ ከፈለጉት ሁሉ አላጣሁም፥ ልቤንም ከደስታ ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ልቤ በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ ዕድል ፋንታዬ ሆነ። 11 እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ፥ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። 12 እኔም ጥበብን፥ ሽንገላንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ ፥ ምክርን የሚከተል፥ ምሳሌንስ ሁሉ የሚያደርግላት ሰው ማን ነው? 13 እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ከአላዋቂ ይልቅ ለብልህ ብልጫ እንዳለው ተመለከትሁ። 14 የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸውና፤ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። 15 እኔም በልቤ፥ “አላዋቂን የሚያገኘው እንዲሁ እኔንም ያገኘኛል፤ እኔም ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ?” አልሁ፤ የዚያን ጊዜም በልቤ፥ “ይህ ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ፥ አላዋቂ በከንቱ መናገርን ያበዛልና። 16 ለብልህ ከአላዋቂ ጋር ለዘለዓለም መታሰቢያ የለውም፤ እነሆ፥ ዘመን ይመጣልና ሁሉም ይረሳል፤ ብልህስ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል? 17 ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ በእኔ ላይ ክፉ ነውና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 18 ከእኔ በኋላ ለሚወለድ ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች እኔ የደከምሁበትን ድካም ሁሉ ጠላሁት። 19 ጠቢብ ወይም አላዋቂ እንደሚሆን ከፀሐይ በታችም በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ይሰለጥን እንደ ሆነ የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 20 እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት። 21 ሰው በጥበብና በዕውቀት በብርታትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ዕድሉን ያወርሳልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው። 22 ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካምና በልቡ ዐሳብ ሁሉ ለሰው አይሆንለትምና፤ 23 ዘመኑ ሁሉ መከራ፥ ቍጣም፥ ቅሚያም ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 24 ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት በድካሙም ለሰውነቱ መልካም ነገር ከሚያሳያት በቀር በጎ ነገር የለም፤ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ። 25 ያለ እርሱ ፈቃድ የሚበላ ወይም የሚጠጣ ማን ነው? 26 እርሱ በፊቱ ደግ ለሆነ ሰው ጥበብንና ዕውቀትን፥ ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኀጢአተኛ ግን በእግዚአብሔር ፊት ደግ ለሆነ ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህ ደግሞ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። |