Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ባሮክ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የኬልቅዩ ልጅ የአሳድዩ ልጅ የሴዴቅያስ ልጅ የማሴው ልጅ የኔርዩ ልጅ ባሮክ ወደ ባቢሎን የጻፈው ነገር ይህ ነው፤ 2 በአምስተኛው ዓመት ከወሩ በሰባተኛው ቀን ከለዳውያን ኢየሩሳሌምን በያዙአትና በእሳት በአቃጠሏት ጊዜ፥ 3 ባሮክ ይህን መጽሐፍ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ጆሮና መጽሐፉን ለመስማት ከሕዝቡ ዘንድ ወደ እርሱ በመጣው ሕዝብ ሁሉ ጆሮ፥ 4 በኀያላኑና በልዑላኑ ጆሮ፥ በሽማግሌዎች ጆሮና ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በባቢሎን በሶዲ ወንዝ አጠገብ በሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ጆሮ አነበበ። 5 እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ ጾሙ፤ ጸለዩም። 6 እያንዳንዳቸውም እንደ እየችሎታቸው ገንዘብ ሰበሰቡ፤ 7 እርሱንም ወደ ሰሉም ልጅ ወደ ኬልቅያ ልጅ ወደ ካህኑ ኢዮአቄም፥ በኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ወደ ነበሩት ካህናትና ወደ ሕዝቡ ሁሉ ላኩት። 8 ከቤተ መቅደስ የተወሰደውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ወደ ይሁዳ ምድር ይመልሱ ዘንድ በሲባን ወር በዐሥረኛው ቀን በወሰዱ ጊዜ ይህም ዕቃ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ ያሠራው የብር ዕቃ ነበር። 9 ይኸውም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢኮንያንንና መኳንንቱን፥ ምርኮኞቹንና ኀያላኑን የሀገሩንም ሕዝብ ይዞ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ከወሰዳቸው በኋላ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም የተጻፈ ደብዳቤ 10 እንዲህም አሉ፥ “እነሆ ገንዘብ ልከንላችኋል፤ በእርሱም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት፤ ዕጣንም ግዙበት፤ ኅብስትም አዘጋጁ፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያም አቅርቡ። 11 ዘመናቸው በምድር ላይ እንደ ሰማይ ዘመን ይሆን ዘንድ ስለ ባቢሎን ንጉሥ ስለ ናቡከደነፆር ሕይወትና ስለ ልጁ ስለ ብልጣሶር ሕይወት ጸልዩ። 12 ለእኛም እግዚአብሔር ኀይልን ይሰጠን ዘንድ፥ ዐይኖቻችንንም ያበራልን ዘንድ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ጥላ ሥርና በልጁ በብልጣሶር ጥላ ሥር በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ለብዙ ዘመንም እንገዛላቸው ዘንድ፥ በፊታቸውም ባለሟልነትን እናገኝ ዘንድ ጸልዩ። 13 አምላካችንን በድለናልና፤ የእግዚአብሔርም መዓቱ መቅሠፍቱም እስከዚች ቀን ድረስ ከእኛ አልተመለሰችምና ለእኛም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን። 14 ወደ እናንተ የላክናትን ይህችንም ደብዳቤ አንብቡአት፤ በበዓል ቀንና በተወደደውም ዕለት በእግዚአብሔር ቤት ተናዘዙ። የኀጢአት ኑዛዜ 15 “እንዲህም በሉ፤ ጽድቅ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ ለእኛ ግን ለፊታችን ኀፍረት ነው፤ ይህች ቀን ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ፥ 16 ለንጉሦቻችንና ለአለቆቻችን፥ ለካህኖቻችንና ለነቢያቶቻችን፥ ለአባቶቻችንም ኀፍረት እንደ ሆነች። 17 በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት በድለናልና፤ 18 አልታዘዝነውምና የአምላካችን የእግዚአብሔርንም ቃል አልሰማንምና፤ በሰጠን በአምላካችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ አልሄድንምና፤ 19 አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ከአወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ አምላካችንን እግዚአብሔርን አልታዘዝነውም፤ ቃሉንም እንዳንሰማ ከእርሱ ራቅን። 20 ወተትና መዓር የምታፈስሰውን ምድር ይሰጠን ዘንድ አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር በአወጣበት ቀን እግዚአብሔር ለባሪያው ለሙሴ ያዘዘው ይህ ክፉ ነገርና መርገም እንደ ዛሬው ዕለት አገኘን። 21 ወደ እኛ እንደ ላካቸው እንደ ነቢያት ቃል የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንም። 22 በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ እናደርግ ዘንድ ለባዕዳን አማልክት እየተገዛን እያንዳንዳችን በክፉ ልባችን ፈቃድ ሄድን። |