ናሆም 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ለነፍሰ ገዳዮች ከተማ፥ ፈጽማ አታላይ ለሆነች፥ በዝርፊያ ለታወቀችና በብዙ ምርኮ ለተሞላች ለነነዌ ከተማ ወዮላት! 2 የአለንጋና የመንኰራኲሮች ድምፅ፥ የፈረስ ግልቢያና የሠረገላ መንጓጓት ይሰማል። 3 ፈረሰኞች ወደፊት እየገፉ የሚያብረቀርቅ ሰይፋቸውንና የሚያብለጨልጭ ጦራቸውን ያነሣሉ፤ ብዙ ሰዎች ስለ ተገደሉ ሬሳዎች ተከምረዋል፤ ከሬሳውም ብዛት የተነሣ በዚያ የሚያልፍ ሰው ሁሉ ይደናቀፋል። 4 ይህም የሆነው ገደብ በሌለው የአምንዝራይቱ ፍትወት ምክንያት ነው፤ እርስዋ በመተት እመቤትነትና በቊንጅናዋ የምታታልልና መንግሥታትን በዝሙትዋ፥ ሕዝቦችን በጥንቈላዋ የምትማርክ ነች። 5 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቼአለሁ፤ ቀሚስሽን ገልቤ ፊትሽን እሸፍናለሁ፤ ሕዝቦች ራቁትነትሽን፥ መንግሥታትም ኀፍረትሽን ያያሉ። 6 የቈሻሻ መጣያ አደርግሻለሁ፤ በንቀት እመለከትሻለሁ፤ ሰው ሁሉ እንዲሳለቅብሽ አደርጋለሁ። 7 የሚያይሽ ሁሉ በመሸማቀቅ ‘እነሆ ነነዌ ፈራርሳ ውድማ ሆናለች፤ ማን ያዝንላታል?’ ይላል። የሚያጽናናትስ እኔ ከወዴት አገኝላታለሁ?” 8 ነነዌ ሆይ! አንቺም የውሃ መከላከያ እንዳለሽ ሁሉ በአባይ ወንዝ አጠገብ ከነበረችው፥ ዙሪያዋ በውሃ ከተከበበው፥ የባሕር ውሃም መከላከያዋ ከሆነው ከግብጽ ከተማ ከቴብስ ትበልጫለሽን? 9 ወሰን የሌለው ኀይልዋ ከግብጽ ከራስዋና ከኢትዮጵያ ይመጣ ነበር፤ የፉጥና ሊብያ ሰዎችም ተባባሪዎችዋ ነበሩ። 10 ይህም ሁሉ ሆኖ የቴብስ ከተማ በጠላት ተይዛ ሕዝቦችዋ ተማርከዋል፤ ሕፃናትዋም በድንጋይ ተፈጥፍጠው በየመንገዱ ወድቀዋል፤ በልዑላኑ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ሹማምንቱንም በሰንሰለት አሰሩአቸው። 11 ነነዌ ሆይ! አንቺም ሰክሮ እንደሚንገዳገድ ሰው የምትሆኚበትና ከጠላቶችሽ ፊት ሸሽተሽ መጠጊያ የምትፈልጊበት ጊዜ ይመጣል። 12 ምሽግሽ ሁሉ ቀድሞ የደረሰ ፍሬ እንደ ተሸከመ የበለስ ዛፍ ይሆናል፤ እርሱ ተነቅንቆ ፍሬው በተራገፈ ጊዜ በበላተኛ አፍ ውስጥ ይወድቃል። 13 ወታደሮችሽ ሁሉ እንደ ሴት ፈሪዎች ሆነዋል፤ የጠረፍሽ በሮች ለጠላቶችሽ ክፍት ሆነዋል፤ መወርወሪያዎቹም እሳት በልቶአቸዋል። 14 ጠላቶችሽ ከበው በሚያስጨንቁሽ ጊዜ የምትጠጪውን ውሃ ቀድተሽ አዘጋጂ! ምሽጎችሽን አጠናክሪ! ጭቃ ረግጠሽ የሸክላ መሥሪያ አዘጋጂ! ጡብም ሥሪ። 15 በእሳት ትቃጠያለሽ ሕዝብሽም በጦርነት ማለቁ አይቀርም፥ በአንበጣ እንደ ተበላ ሰብል ትጠፊያለሽ፤ ስለዚህ እንደ አንበጣና እንደ ኲብኲባ ተባዙ። 16 ነጋዴዎችሽ ከሰማይ ከዋክብት ይበልጥ በዝተዋል፤ ነገር ግን እንደ አንበጣ ምድሪቱን ግጠው በረው ይሄዳሉ። 17 ጠባቂዎችሽ እንደ ኲብኲባ፥ ባለ ሥልጣኖችሽ በብርድ ቀን በአጥር ላይ እንደ ሰፈረ የአንበጣ መንጋ ናቸው፤ ፀሐይ ሲወጣ በረው ይሄዳሉ፤ ወዴት እንደሚሄዱ ግን የሚያውቅ የለም። 18 የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ ጠባቂዎችህ ተኝተዋል፤ ልዑላንህ አንቀላፍተዋል፤ ሕዝብህ በተራራ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሰበስባቸውም የለም። 19 ክፉኛ የተጐዳሽ ስለ ሆነ ቊስልሽን ሊፈውስ የሚችል ነገር የለም፤ ማለቂያ ከሌለው ከአንቺ የጭካኔ ድርጊት ያመለጠ ሰው ስለሌለ ስለ አንቺ የሚሰሙ ሁሉ በአንቺ መውደቅ ያጨበጭባሉ። |