ማርቆስ 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰዱ ( ማቴ. 27፥1-2 ፤ 11-14 ፤ ሉቃ. 23፥1-5 ፤ ዮሐ. 18፥28-38 ) 1 ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሸንጎውም አባሎች ሁሉ ጋር ተማከሩ፤ ከዚያም በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። 2 ጲላጦስም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው፤” አለው። 3 የካህናት አለቆች ግን ኢየሱስን በብዙ ይወነጅሉት ነበር። 4 ስለዚህ ጲላጦስ “በስንት ነገር እንደሚከሱህ ተመልከት! ከቶ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል እንደገና ጠየቀው። 5 ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ አሁንም ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጠም። ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ( ማቴ. 27፥15-26 ፤ ሉቃ. 23፥13-25 ፤ ዮሐ. 18፥39-40 ፤ 19፥1-16 ) 6 ጲላጦስ በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሰዎቹ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ይለቅላቸው ነበር። 7 በዚያን ጊዜ በመንግሥት ላይ ተነሣሥተው፥ ሰው በመግደል ወህኒ ቤት የገቡ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከነዚህም ዐመፀኞች አንዱ በርባን የሚባለው ሰው ነበር። 8 ሕዝቡም ወደ ጲላጦስ ቀርበው የተለመደውን ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠየቁት። 9 እርሱም “የአይሁድን ንጉሥ ፈትቼ እንድለቅላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። 10 ይህንንም ያለው የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ስለ ነበር ነው። 11 የካህናት አለቆች ግን፥ “በእርሱ ፈንታ በርባን ይፈታልን፤” ብለው ጲላጦስን እንዲጠይቁ ሰዎቹን አነሣሡ። 12 ጲላጦስም፦ “ታዲያ፥ ይህን የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላድርገው?” ሲል ሰዎቹን እንደገና ጠየቀ። 13 እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ እንደገና ጮኹ። 14 ጲላጦስም “ለምን? ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። 15 ጲላጦስ ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን አስገረፈውና እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮች በኢየሱስ ማፌዛቸው ( ማቴ. 27፥27-31 ፤ ዮሐ. 19፥2-3 ) 16 ወታደሮቹ ኢየሱስን ወደ አገረ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ የቀሩትንም ወታደሮች ሁሉ ጠሩ፤ 17 ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበትና፤ 18 “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ በማፌዝ እጅ ይነሡት ነበር። 19 በመቃ ራስ ራሱን ይመቱት ነበር፤ ምራቃቸውንም እንትፍ ይሉበት ነበር፤ በፊቱም በማላገጥ እየተንበረከኩ ይሰግዱለት ነበር። 20 ካፌዙበትም በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው፥ የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። የኢየሱስ መሰቀል ( ማቴ. 27፥32-44 ፤ ሉቃ. 23፥26-43 ፤ ዮሐ. 19፥17-27 ) 21 ሲሄዱም ሳሉ የቀሬና ሰው የሆነውን የእስክንድርንና የሩፎስን አባት ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። 22 ከዚያም በኋላ ኢየሱስን ትርጒሙ የራስ ቅል ወደ ሆነው ስፍራ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። 23 እዚያም ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልጠጣም። 24 ከዚህም በኋላ ሰቀሉት፤ ልብሶቹንም ማን ምን እንደሚወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት። 25 ኢየሱስን ሲሰቅሉት ጊዜው ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። 26 ወንጀሉንም ለማመልከት “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር። 27 ከኢየሱስም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አምጥተው አንዱን በቀኙ፥ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። [ 28 በዚህም ሁኔታ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤” የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጸመ።] 29 በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች ራሳቸውን በንቀት እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር፦ “አዬ፥ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው! 30 እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” 31 በዚህ ዐይነት የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራንም እርስ በርሳቸው እንዲህ እየተባባሉ ይዘባበቱበት ነበር፦ “ሌሎችን አድኖአል፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! 32 እርሱ መሲሑ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንይና እንመንበት!” እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር። የኢየሱስ ሞት ( ማቴ. 27፥45-56 ፤ ሉቃ. 23፥44-49 ፤ ዮሐ. 19፥28-30 ) 33 ከቀኑም ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 34 ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። 35 በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ የእርሱን ጩኸት ሰምተው “እነሆ! ኤልያስን ይጠራል፤” አሉ። 36 ከእነርሱም አንዱ ሮጠና ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ፤ እንዲጠጣውም በመቃ ላይ አድርጎ ለኢየሱስ ሰጠውና “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደ ሆነ እንይ!” አለ። 37 ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ነፍሱም ከሥጋው ተለየች። 38 የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። 39 በመስቀሉ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረ የመቶ አለቃ ኢየሱስ እንዴት ነፍሱ ከሥጋው እንደ ተለየች ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፤” አለ። በጎልጎታ የነበሩ ሴቶች ( ማቴ. 27፥55-56 ፤ ዮሐ. 19፥25-27 ) 40 በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ፥ አንዳንድ ሴቶችም በዚያ ነበሩ። ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፥ ሰሎሜም ይገኙ ነበር። 41 እነርሱ ኢየሱስ በገሊላ በነበረበት ጊዜ፥ ይከተሉትና ያገለግሉት ነበር። እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ብዙ ሌሎች ሴቶች ነበሩ። የኢየሱስ መቀበር ( ማቴ. 27፥57-61 ፤ ሉቃ. 23፥50-56 ፤ ዮሐ. 19፥38-42 ) 42 ቀኑ መሽቶ ስለ ነበር የሰንበት ዋዜማና የዝግጅትም ጊዜ ሆነ፤ 43 በዚያኑ ጊዜ የአይሁድ ሸንጎ አባል የነበረ ዮሴፍ የሚባል፥ የተከበረ የአርማትያስ ሰው መጣ። እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበር። በድፍረት ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ለመነ። 44 ጲላጦስም “እንዴት እንዲህ በቶሎ ሞተ?” ብሎ ተደነቀ። የመቶ አለቃውንም አስጠርቶ፥ “በእርግጥ ከሞተ ቈይቶአልን?” ሲል ጠየቀው። 45 የኢየሱስን መሞት ከመቶ አለቃው ከሰማ በኋላ አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት። 46 ዮሴፍ አዲስ የከፈን ልብስ ገዛና የኢየሱስን አስከሬን ከመስቀል አውርዶ ገነዘው፤ ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው። ትልቅ ድንጋይም አንከባሎ መቃብሩን ዘጋ። 47 መግደላዊት ማርያምና የዮሳ እናት ማርያም ኢየሱስን የት እንደ ቀበሩት ይመለከቱ ነበር። |