መሳፍንት 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሳምሶን የፍልስጥኤማውያንን እህል ማቃጠል 1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ለማየት ሄደ፤ እርሱም፥ “ሚስቴ ወዳለችበት ጫጉላው ቤት ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም። 2 አባትየውም፥ “ፈጽሞ የጠላሃት መሆንህን ስለ ተረዳሁ ለሚዜህ ድሬለታለሁ፤ ታናሽ እኅቷ ከእርሷ ይልቅ ውብ አይደለችምን? እርሷን አግባት” አለው። 3 ሳምሶንም መልሶ፥ “ከእንግዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ በሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ አልሆንም” አላቸው። 4 ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋር አሰረው። 5 ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ። 6 ፍልስጥኤማውያን፥ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፥ “ሚስተ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የቲምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ። ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው። 7 ሳምሶንም፥ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ። 8 ክፉኛ መታቸው፤ ከነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኢታም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ። የአህያ መንጋጋ 9 ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ። 10 የይሁዳም ሰዎች፥ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ልና ስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው። 11 ከዚያም ሦስት ሺህ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤታም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፥ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። ሳምሶንም፥ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረ ጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው። 12 እነርሱም፥ “አስረን ለፍልስጥአማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት። ሳምሶንም፥ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው። 13 እነርሱም፥ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት። 14 ሳምሶን ሌሒ እንደደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የጌታ መንፈስ በሳምሶን ላይ በኃይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ። 15 ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺህ ሰው ገደለ። 16 ሳምሶንም፥ “በአንድ የአህያ መንጋጋ፥ ሺህ ሰው ዘራሪ፤ በአንድ የአህያ መንጋጋ፥ ሺህ ሬሳ አነባባሪ!” ብሎ ፎከረ። 17 ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒሰ ተብሎ ተጠራ። 18 እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ?” በማለት ወደ ጌታ ጮኸ። 19 እግዚአብሔርም በሌሒ ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውኃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ። ስለዚህ ያ ምንጭ ዓይንሀቆሬሸ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው በሌሒ ይገኛል። 20 ሳምሶንም በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅቀ ሆነ። |