Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሁለቱ ንስሮችና የወይን ተክል

1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ፥ እንቆቅልሽ ጠይቅ፥ ለእስራኤልም ቤት ምሳሌን መስል፥

3 እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትልቅ ክንፎች፥ ረጅም ማርገብገቢያ ያለው፥ ዝንጉርጉርና ብዙ ላባ ያለው ትልቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ።

4 ቀንበጡንም ቀነፈ፥ ወደ ከነዓንም ምድር አመጣው፥ በነጋዴዎችም ከተማ ተከለው።

5 ከምድሪቱም ዘር ወሰደ፥ በመልካም መሬትም አኖረው፥ በብዙ ውኃ አጠገብም እንደ አኻያ ዛፍ ተከለው።

6 በበቀለም ጊዜ ቁመቱ አጭር፥ ሐረጉ ወደ እርሱ የሚመለስ፥ ሥሮቹም በበታቹ የነበሩት ሰፊ ወይን ሆነ፥ ወይንም ሆነ፥ ቅርንጫፎችን አበቀለ፥ ቅጠልም አወጣ።

7 ትልልቅ ክንፎችና ብዙ ላባ ያለው ሌላ አንድ ትልቅ ንስር ነበረ፥ እነሆም ይህ ወይን እንዲያጠጣው ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ፥ ቅርንጫፉንም ከተተከለበት ከመደብ ወደ እርሱ ሰደደ።

8 ቅርንጫፍ እንዲያወጣ፥ ፍሬ እንዲያፈራ፥ የተዋበ ወይን እንዲሆን ብዙም ውኃ ባለበት በመልካም መሬት ውስጥ ተተክሎ ነበር።

9 እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያድግ ይሆንን? እንዲደርቅ፥ አዲስ የበቀለው ቅጠሉም እንዲጠወልግ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አያረግፈውምን? ከሥሩም ለመንቀል ብርቱ ክንድ ወይም ብዙ ሕዝብ አያስፈልገውም።

10 እነሆ ሲተከልስ ያድግ ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ በመታው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።

11 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

12 ለዓመፀኛ ቤት እንዲህ በል፦ እነዚህ ነገሮች ምን እንደ ሆኑ አታውቁምን? በላቸው። ንገራቸው፦ እነሆ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና ልዑሎችዋን ወሰደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ባቢሎን አመጣቸው።

13 ከንጉሣውያን ቤተሰብ አንዱን ዘር ወስዶ ከእርሱ ቃል ኪዳን ጋር አደረገ፥ አማለውም፥ የምድሪቱንም አለቆች ወሰደ፤

14 ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ ይህች መንግሥት እንድትዋረድና እራስዋን ከፍ እንዳታደርግ ነው።

15 ነገር ግን በእርሱ ላይ ዐመጸ፥ ፈረሶችንና ብዙ ሕዝብም እንዲሰጡት መልእክተኞቹን ወደ ግብጽ ላከ። ይሳካለታልን? እነዚህን ነገሮች ያደረገስ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንን አፍርሶስ ያመልጣልን?

16 እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ መሐላውን የናቀበት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውን ቃል ኪዳኑን ያፈረሰበት፥ ያነገሠው ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል።

17 ብዙ ነፍሳትን ለማስወገድ ጉብታ በደለደሉ፥ ቅጥርንም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከኃያል ሠራዊቱና ከታላቅ ጉባኤው ጋር በጦርነት አይረዳውም።

18 መሐላውን ስለ ናቀ፥ ቃል ኪዳኑንም ስላፈረሰ፥ እነሆም እጁን ሰጠ፥ እነዚህንም ሁሉ አደረገ፥ ስለዚህ አያመልጥም።

19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ።

20 መረቤን በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ፥ በዚያም በእኔ ላይ ለፈጸመው ክሕደት ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ።

21 የሚያመልጡ ወታደሮቹ ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፥ እኔም ጌታ እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ።


የእስራኤል በመጨረሻ ከፍ ማለት

22 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ራሴ ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አስቀምጠዋለሁ፥ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፥ በረጅምና ከፍ ያለ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ።

23 ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል፥ ፍሬም ያፈራል፥ የተዋበ ዝግባ ይሆናል፥ በበታቹም ወፎች ሁሉ ይኖራሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርሩ ሁሉ ይቀመጣሉ።

24 የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርጋለሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos