Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ባሮክ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በእግዚአብሔር ፊት በፈጸማችሁት በደል ምክንያት በባቢሎናውያን ንጉሥ በናቡከደነፆር ተማርካችሁ ወደ ባቢሎን ትወሰዳላችሁ። 2 ወደ ባቢሎን በደረሳችሁ ጊዜ እዚያ ብዙ ዓመታት ትቆያላችሁ፥ እስከ ሰባት ትውልድ። ከዚህ በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራችሁ በሰላም እንድትሄዱ አደርጋችኋለሁ። 3 ሰው በትከሻው የሚሸከማቸው ሕዝቦችን የሚያስፈሩ፥ በብር፥ በወርቅ፥ በእንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች በባቢሎን ታያላችሁ። 4 በዚያን ጊዜ ተጠንቀቁ፥ እናንተ በምንም ዓይነት የሌላ አገር ሰዎችን እንዳትመስሉ፥ የእነርሱን አማልክቶቻቸውን አትፍሩ፥ 5 በጣዖቶቹ ፊትና ኋላ ሰዎች ሲሰግድ ስታዩ አትደንግጡ፥ ይልቁንም በልባችሁ “ጌታ ሆይ አንተን እናመልካለን” በሉ። 6 ምክንያቱም የእኔ መልአክ ከእናንተ ጋር ነው። ሕይወታችሁ በእርሱ ጥላ ሥር ነው። 7 በእርግጥ የእነዚህ ጣዖቶች ምላስ ተጠርቦ የተሠራው በአንድ ሠራተኛ ነው፥ እውነት ነው፥ ጣዖቶች በወርቅና በብር ተለብጠው ተሠርተዋል፥ ነገር ግን የውሸት ናቸው፥ መናገርም አይችሉም። 8 ማጌጥን እንደምትወድ ልጃገረድ እነዚህ ሰዎችም ወርቅ ይወስድና 9 በአማልክቶቻቸው ራስ ላይ ዘውድ ይደፋሉ። እንዲያውም ካህናት እንኳ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ወርቁንና ብሩን ይወስዳሉ፥ 10 ወርቁንና ብሩን በጠላቶቻቸው ቤት ለሚያገለግሉ ሴተኛ አዳሪዎችም እስከ መስጠት ይደርሳሉ፥ እነዚህን የብር፥ የወርቅና የእንጨት ጣዖቶች እንደ ሰዎች ያለብሷቸዋል። 11 የከፋይ ካባ የደረቡ እንኳን ቢሆኑም ጣዖቶቹ እራሳቸውን ከመዛግና ከመበላሽት፥ ከሚቦሮቡሩአቸው ትሎች አያድኑም፥ 12 በመኖሪያቸው የቤተ መቅደሱ አቧራ ፊታቸውን ስለማያለብሰው ሁልጊዜም አቧራው ከፊታቸው ላይ መጠረግ አለበት። ጣዖቱ የአንድ አውራጃ ገዢ ሆኖ በትረ መንግሥትን ጨብጦ፥ ነገር ግን ሥልጣኑን የሚፈታተነውን ሰው በሞት መቅጣት የሚሳነውን ሰው ይመስላል። 13 በቀኝ እጅ ሰይፍና መጥረቢያ ይይዛል። ግን በጦርነት እና ሽፍታ በሚመጣበት ጊዜ ለመከላከያ አይጠቅሙትም። 14 አምላክ አለመሆናቸ በዚህ ይታወቃል፥ ስለዚህ አትፍሩአቸው። 15 እንስራ ከነቃ ጥቅም እንደሌለው ሁሉ፥ 16 በቤተ መቅደስ የተኰለኰሉ አማልክትም እንደዚሁ ናቸው፥ ሰው ሲራመድ በሚነሣው አቧራ የተሸፈኑ ናቸው፥ 17 ንጉሥን በመስደቡ ሞት የተፈረደበት ሁሉ በእስር ቤት እንደሚዘጋበት እንዲሁም የጣዖት አገልጋዮች እነዚህ ጣዖቶች በሌቦች እንዳይዘረፉ የጣዖት ቤቶችን በመዝጊያዎች፥ በቁልፎች፥ በብረት ዘንጐች አጥብቀው ይዘጋሉ። 18 የጣዖት አገልጋዮቹ ለራሳቸው ከሚገባቸው በላይ ለጣዖቶቹ በርካታ መቅረዞች ያበራሉ፤ ነገር ግን ጣዖቶቹ አንዳቸውም አያዩም። 19 በጣዖት ቤቱ እንደሚገኘው፥ ውስጡ በምስጥ እንደተበላው ግንድ ይመስላሉ፥ ከምድር የሚመጣው ምስጥ እነሱን፥ ልብሳቸውንም ይበላል፤ እነሱ አይሰሙትም። 20 ከጣዖት ቤቱ በሚወጣው ጢስ ፊቱን አክስሎታል። 21 በአካላቸውና በራሳቸው ላይ የሌሊት ወፎችና ንቦች ያርፋሉ፤ ድመቶችም እንዲሁ፥ 22 አምላክ አለመሆናቸውን የምታውቁት በዚህ ነው፤ ስለዚህ አትፍሩአቸው። 23 እነርሱን ለማሳመር በእነርሱ ላይ የተለበጠው ወርቅም ቆሻሻውን ሰው ካልወለወለው እነሱ አጽድተው ንጹሕ ሊያደርጉት አይችሉም፤ ሊሠሩአቸው በብረት ማቅለጫ ውስጥ ሲያስገቧቸውም አይሰሙም ነበረ። 24 ምን ያክል ውድ ዋጋ ቢከፈልባቸውም እስትፋስም ሆነ ሕይወት ፈጽሞ የለባቸውም፥ 25 መራመድ ስለማይችሉ ሰው በትከሻው ይሸከማቸዋል። ይህም ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደ ሆኑ ያሳያል። ቢወድቁ እንኳ የሚያነሳቸውን አምላኪዎቻቸውን ምን ያህል ያሳፍሩአቸዋል፥ 26 አንዴ ከቆሙ በራሳቸው መነቃነቅ አይችሉም፥ እራሳቸውን ማስተካከል አይችሉም፥ ለእነርሱ የሚቀርብ መሥዋዕት ለሙታን እንደሚቀርብ ያህል ነው። 27 ጣዖቶች የሚቀርቡትን ምንም ዓይነት መሥዋዕቶች፥ የጣዖት አገልጋዮቹ ሸጠው ገንዘቡን ለግላቸው ያደርጉታል፤ ሚስቶቻቸውም እንዲሁ ደግሞ የትርፉን ከፊል ይወስዳሉ፤ ነገር ግን ለድሆችና ረዳት ለሌላቸው ምንም አይለግሱም፤ 28 በወር አበባዋ ጊዜ ያለች፥ እንዲሁም እመጫት ሴት ለጣዖቶች የቀረቡትን መሠዋዕቶች ይነካሉ። ይህን ሁሉ ስትመለከቱ አምላክ አለመሆናቸውን ስለምታውቁ አትፍሩአቸው። 29 እነኚህን የብር የወርቅ፥ የእንጨት አማልዕክት የሚያገለግሏቸው ሴቶች ከሆኑ ታዲያ እንዴት ተብሎ አምላክ ይባላሉ? 30 የጣዖት አገልጋዮች የተቀደደ ልብስ ለብሰው፥ ራሳቸውንና ጢማቸውን ሳይሸፍኑ በቤተ መቅደሱ ይቀመጣሉ፥ 31 በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚያደርጉት ሆነው በጣዖቶቻቸው ፊት ያጓራሉ፥ ይጮሃሉ። 32 የጣዖት አገልጋዮቹ የጣዖቶቹን ልብስ ወስደው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ያለብሳልሉ። 33 ደግ ቢደረግላቸው ወይም ክፉ ሲደረግባቸው እነዚህ ጣዖቶች መልሰው ብድር መክፈል አይችሉም፤ ንጉሥ መሾም ወይም መሻር እንደማይችሉ ሁሉ ሀብትንና ገንዘብንም ማከፋፈል ይሳናቸዋል። 34 ሰው በመሐላ የገባላቸውን ቃል ሳይፈጽመው ቢቀር አይተሳሰቡትም። 35 ማንንም ከሞት አያድኑም፤ ደካማውን ከኃይለኛ ሰው አያድኑትም፥ 36 የዕውሩን ዐይን አያበሩም፤ በመከራ ላይ የሚገኘውን ሰው ከመከራ አያወጡትም፤ 37 ለመበለቶች አይራሩም፤ ወላጆች ለሞቱበት ልጅ መልካም ነገር አያደርጉለትም። 38 በወርቅና በብር የተለበጡ እነዚህ የእንጨት አማልዕክቶች ከተራራ ከወደቀ ሥር ዓለት አይሻሉም፤ የሚያገለግሏቸውም ሰዎች እፍረትን ያከናነባሉ። 39 ታዲያ እንዴት ተደርጐ አምላክ ናቸው ለማለት ይቻላል? 40 ከለዳውያን (ባቢሎናውያን) ራሳቸው ያዋርዷቸዋል፤ መናገር የማይችል ሰው ሲያገኙ ወደ ተባለው ጣዖት ይወስዱታል፤ ጣዖቱ የመናገርን ስጦታ መስጠት እንደሚችል፤ ችግሩ እንደሚገባው ቆጥረው ወደ እሱ ፊት ያቀርቡታል። 41 ከዚህ በመነሣት አማልክቱን መተው እንደሚገባቸው አይረዱም፤ የአመለካከት አድማስ ማነስ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። 42 ሴቶች ገመድ ታጥቀው ገለባውን እንደ ዕጣን ለማጨስ በመንገድ ላይ ይቀመጣሉ፤ 43 ከነኝህም ሴቶች መካከል አንዲቱ በአንድ መንገደኛ ተወስዳ ግንኙነት ብታደርግ ከሌሎቹ ሁሉ ገመድን በማስበጠስ እራሷን የተሻለች አድርጋ ታቀርባለች። 44 ምንም ቢደረግላቸው ድርጊቱ ውሸት ነው። ታዲያ እንዴት አምላክ ናቸው ይባላሉ? 45 በእንጨት ጠራቢዎችና በወርቅ አፍሳሾች የተሠሩ ናቸው፥ እነርሱ ባለሙያዎቹ እንደ ፈለጉት ይሆናሉ እንጂ ሌላ ነገር መሆን አይችሉም። 46 እነዚህ የሠሩአቸው ሰዎች እንኳ ረጅም ዕድሜ አይኖሩም። 47 እንዴት ታዲያ በነሱ የተሠሩ ነገሮች አምላክ መሆን ይችላሉ? ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ለትውልዳቸው ውሸትንና እፍረትን ይተዋሉ። 48 ጦርነትና ችግር ሲመጣ የጣዖቱ ካህናት እነዚህን ጣዖቶች ይዘው የት መደበቅ እንደሚገባቸው እርስ በእርሳቸው ይመካከራሉ። 49 ራሳቸውን ከጦርነትና ከችግር ማዳን የማይችሉትን እንዴት አምላክ አለመሆናቸውን ማወቅ ያቅታቸዋል? 50 በወርቅና በብር የተለበጡ የእንጨት ዕቃዎች ናቸው፤ ውሸት ብቻ መሆናቸው በዚህ ይታወቃል፤ በሰው እጅ የተሠሩ እንጂ አምላክ አለመሆናቸው ለንጉሦችና ለሕዝቦች ሁሉ ግለጽ ይሆናል፤ በነሱ ምንም የአምላክ ሥራ አለመኖሩ ግልጽ ይሆናል። 51 ታዲያ እነሱ አምላክ አለመሆናቸውን ለመቀበል የማይገደድ ማነው? 52 ለአንድ አገር ንጉሥ አይሾሙለትም፤ ለሰዎች ዝናብም አያወርዱም። 53 ምንም ኃይል ስለ ሌላቸው እነሱን የሚመለከቱ ጉዳዮችን መመልከትና መቆጣጠርም አይችሉም፥ ክፉ ነገር የተሠራበትንም ሰው አይረዱም። 54 በእነዚህ በወርቅና በብር በተለበጡ የእንጨት ጣዖቶች ቤተ መቅደስ ላይ እሳት ቢወድቅ፥ የጣዖቶቹ አገልጋዮች ሸሽተው ያመልጣሉ፤ እነርሱ ግን በእሳት ውስጥ እንደሚገኙ ምሰሶ በሙሉ ተቃጥለው ያልቃሉ። 55 ንጉሥን ወይም ጠላቶችን መከላከል አይችሉም፤ 56 ታዲያ እነሱን አምላክ ናቸው ብሎ መቀበል እንዴት ይቻላል? 57 በብርና በወርቅ የተለበጡ የእንጨት ጣዖቶች ከሌባም ሆነ ከወንበዴዎች ራሳቸውን አያድኑም፤ ጉልበተኞች ወርቃቸውንና ብራቸውን ቢወስዱባቸውና የለበሱትም ቢገፏቸው ራሳቸውን እንኳን ከዚህ ጥቃት ለማዳን ምንም ኃይል የላቸውም። 58 እንደ እነዚህ የውሸት አማልክት ከመሆን ይልቅ ጀግንነቱን እንደሚያሳይ ንጉሥ፥ በቤት ውስጥ ባለቤቱ የሚጠቀምበት ጠቃሚ እንስራ መሆን ይመረጣል። ወይም ደግሞ በውስጥ ያለውን ነገር የሚጠብቅ የቤት መዝጊያ ይሻላል፥ ወይም ከእነዚህ ከውሸት ጣዖቶች ይልቅ በቤተ መንግሥት የሚገኝ የእንጨት ምሰሶ ይሻላል። 59 ብርሃን የሚሰጡት ፀሐይ፥ ጨረቃና ከዋክብት የሚሠሩት ሥራ ተሰጥቷቸዋል፤ ታዛዦችም ናቸው። 60 መብረቅም ብልጭ ሲል እንዲሁ መልካም ይታያል፤ 61 በተመሳሳይ መልኩ ንፋስ በየሃገሩ ይነፍሳል፤ ደመናዎች መሬት እንዲያካልሉ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። 62 ከላይ የወረደው እሳት ጫካውንና ተራራውን እንዲያቃጥል የተሰጠውን ትእዛዝ ይፈጽማል፤ እነኚህ ጣዖቶች ግን ከላይ ከተጠቀሱት ጋር አይወዳደሩም፤ በውበትም ሆነ በኃይል ወይም ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ምንም ችሎታ የላቸውም። 63 በመሆኑም እነርሱን አምላክ ብሎ መጥራት ፈጽሞ አይታሰብም፤ ፍርድ መፍረድ ሆነ ማንንም መርዳት አይችሉም። 64 እነሱን አምላክ አለመሆናቸውን እወቁ፤ ስለዚህ አትፍሩአቸው። 65 እነሱ ንጉሦቹን መርገምም ሆነ መመረቅ አይችሉም፤ 66 ለሕዝቦች በሰማይ ላይ ምልክቶች ማሳየት አይችሉም፤ እንደ ፀሐይ ብርሃን መፈንጠቅ ወይም እንደ ጨረቃ ብርሃን ማንጸባረቅ አይችሉም። 67 ወደ አንድ መጠጊያ ቦታ ሸሽተው ራሳቸውን በራሳቸው መርዳት የሚችሉ የዱር አራዊቶች ይበልጧቸዋል። 68 ስለዚህ በምንም ዓይነት አምላክ ለመሆናቸው ማስረጃ የለም፤ ሰለዚህ አትፍሩአቸው። 69 በብርና በወርቅ የተለበጡ የእንጨት ጣዖቶቻቸው በዱባ እርሻ ውስጥ እንደሚገኝ ከምንም እንደሚያድን በሰው ምስል የቆመ የእንጨት ማስፈራሪያ ናቸው። 70 ወይም በአትክልት ስፍራ እንደሚገኘውና ማንኛውም ዓይነት ወፍ እንደሚያርፍበት የእሾህ ቁጥቋጦ ናቸው፤ ወይም ደግሞ ጨለማ ውስጥ የተጣለ ሬሳ ይመስላሉ። 71 የከፋዩ ልብሳቸው ብልጭልጭነት ሲበላሽ ስታዩ አምላክ አለመሆናቸው ይገባችኋል። በመጨረሻም እነዚህ ዕቃዎች ምስጥ በልቶ ይጨርሳቸውና የአገር ውርደት ይሆናሉ። 72 ትክክለኛና ጣዖት የሌለው ሰው ይሻላል፤ ውርደት በፍፁም ወደሱ አይጠጋምና። |