ሉቃስ 6:20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዐይኖቹን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ድሆች፥ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንተ ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። |
ነዳያን ደስታቸውን በእግዚአብሔር ያበዛሉ፤ በሰዎች መካከል ተስፋ የሌላቸውም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ።
ይህ ሁሉ የእጄ ሥራ ነው፤ ይህም ሁሉ የእኔ ነው፥” ይላል እግዚአብሔር፤ “ወደ የዋሁና ወደ ጸጥተኛው፥ ከቃሌም የተነሣ ወደሚንቀጠቀጥ ሰው ከአልሆነ በቀር ወደ ማን እመለከታለሁ?
አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን፥ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት በአያችኋቸው ጊዜ እናንተን ወደ ውጭ ያወጡአችኋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
አብርሃም ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ተድላና ደስታ እንዳደረግህ፥ አልዓዛርም እንዲሁ ሁልጊዜ በችጋር እንደ ነበረ ዐስብ፤ አሁን ግን እንዲሁ እርሱ በዚህ ፈጽሞ ተድላና ደስታ ያደርጋል፤ አንተ ግን መከራ ትቀበላለህ።
“የእግዚአብሔር መንፈስ በላዬ ነው፤ ስለዚህ ቀብቶ ለድሆች የምሥራችን እነግራቸው ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፥ ያዘኑትንም ደስ አሰኛቸው ዘንድ፥ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፥ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የታሰሩትንም እፈታቸው ዘንድ፥ የቈሰሉትንም አድናቸው ዘንድ፥
የደቀ መዛሙርትንም ልቡና አጽናኑ፤ በሃይማኖትም እንዲጸኑ፦“ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” እያሉ መከሩአቸው።
ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስተኞች ነን፤ እንደ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን እናበለጽጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ በእጃችን ነው።
በብዙ መከራ ከመፈተናቸው የተነሣ ደስታቸው በዝቶአልና፤ በድህነታቸው ጥልቅነትም የለጋስነታቸው ባለጠግነት በዝታለችና።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለ እናንተ ራሱን ድሃ አደረገ።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን?
“መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።
ችግረኛውን ከመሬት ያነሣዋል፤ ምስኪኑንም ከጕድፍ ያነሣዋል፤ ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጠው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሰው ዘንድ።