ኤርምያስ 3:1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? አንቺም ከብዙ እረኞች ጋር አመንዝረሻል፤ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣ እርሷም ሄዳ ሌላ ሰው ብታገባ፣ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ምድሪቱስ ፈጽማ አትረክስምን? አንቺ ግን ከብዙ ወዳጆችሽ ጋራ አመንዝረሻል፤ ታዲያ አሁን ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽን?” ይላል እግዚአብሔር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነሆ፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ብትሄድ ሌላም ወንድ ብታገባ፥ በውኑ በድጋሚ ወደ እርሷ ይመለሳልን? ያች ምድር እጅግ የረከሰች አትሆንምን? አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል ጌታ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ እርስዋም ከእርሱ ተለይታ ሌላ ወንድ ካገባች በኋላ እንደገና መልሶ ሊያገባት ይችላልን? ይህ ቢደረግማ ፈጽሞ ምድርን የሚያረክስ ይሆናል። እስራኤል ሆይ! አንቺ ግን ብዙ ጣዖቶችን ወደሽ ነበር፤ አሁን ደግሞ እንደገና ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በሰው ዘንድ፦ ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? ይባላል። አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። |
ምድርም በሚቀመጡባት ሰዎች ምክንያት በደለች፤ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዐቱንም ለውጠዋልና፥ የዘለዓለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና።
ከጥንት ጀምሬ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ፤ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፤ አንቺም፦ አላገለግልም አልሽ፤ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፤ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ።
አንቺስ፦ አልረከስሁም፤ በዓሊምንም አልተከተልሁም፤ እንዴት ትያለሽ? በሸለቆ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፤ ያደረግሽውንም ዕወቂ። ማታ ማታ በመንገዶች ትጮኻለች፤
ፍሬዋንና በረከቷንም ትበሉ ዘንድ ወደ ቀርሜሎስ አገባኋችሁ፤ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፤ ርስቴንም አጐሳቈላችሁ።
“ከዳተኞች ልጆች ሆይ! ተመለሱ፤ ቍስላችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ እኛ አገልጋዮችህ እንሆናለን፤ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና።
አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሰው ወደ ድኅነት ይመጣል።”
ቤት። በሌሊት እጅግ ታለቅሳለች፤ እንባዋም በጉንጭዋ ላይ አለ፤ ከሚያፈቅሩአት ሁሉ የሚያጽናናት የለም፤ ወዳጆችዋም ሁሉ ወነጀሉአት፤ ጠላቶችም ሆኑአት።
አካላቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብፃውያን ልጆች ጋር አመነዘርሽ፤ እኔንም ታስቆጭ ዘንድ ዝሙትሽን አበዛሽ።
“ይህን ሁሉ የሴሰኛ ሴት ሥራን ሠርተሻልና፥ ከሴቶች ልጆችሽም ጋር ሦስት ጊዜ አመንዝረሻልና ሴቶች ልጆችሽን ምን አደርጋቸዋለሁ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
እኔ ሕያው ነኝና ኀጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኀጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር የቃሉ መጀመሪያ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሆሴዕን፥ “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታመነዝራለችና ሂድ፤ ዘማዊቱን ሴትና የዘማዊቱን ልጆች ለአንተ ውሰድ” አለው።
እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና እናታችሁን ተዋቀሱአት። ዝሙቷን ከፊቷ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል አስወግዳለሁ።
ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ተመለሱ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ብላቴናዪቱን ወደ አባቷ ቤት ደጅ ያውጡአት፤ በእስራኤልም ዘንድ ስንፍናን አድርጋለችና፥ የአባቷንም ቤት አስነውራለችና የከተማው ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሉአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።