ዘፀአት 40:35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ደመናውም በላዩ ስለነበር ድንኳኑም የእግዚአብሔርን ክብር ስለ ተሞላ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ደመናው በላዩ ላይ ስለ ነበረና የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላው፣ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ደመናው በላዩ ስለ ነበረና የጌታ ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ደመናው ስለረበበበትና የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ስለ ሞላው ሙሴ ወደ ድንኳኑ ለመግባት አልቻለም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። |
የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ በዚያች ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም።
አሮንም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ።
እግዚአብሔርም ይመጣል፤ በጽዮን ተራራ ላይ ባለ ቦታ ሁሉ፥ በዙሪያውም ላይ ደመና በቀን እንደ ጢስ፥ በሌሊትም እንደሚቃጠል የእሳት ብርሃን ይጋርዳል፤ በክብርም ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናል።
ለዘለዓለም በአርያም የሚኖር ስሙም ቅዱሰ ቅዱሳን የሆነ፥ በቅዱሳን አድሮ የሚኖር፥ ለተዋረዱት ትዕግሥትን የሚሰጥ፥ ልባቸውም ለተቀጠቀጠ ሕይወትን የሚሰጥ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
የእግዚአብሔር ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መድረክ ላይ ቆመ፤ ቤቱም በደመናው ተሞላ፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ፀዳል ተሞላ።
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው።
ሙሴም ወደ ምስክሩ ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው በላይ ከኪሩቤልም መካከል የእግዚአብሔርን ድምፅ ይሰማ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ይናገር ነበር።
ድንኳንዋን በተከሉበት ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈናት፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በድንኳኑ ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር።
ከእግዚአብሔርም ክብርና ከኀይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፤ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ እንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም።