ዘኍል 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የፋሲካ በዓል በሲና ስለ መከበሩ 1 የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ። 3 በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዐቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት።” 4 ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። 5 በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ። 6 በሰውነታቸው ርኵሰት የነበረባቸው ሰዎች መጡ፤ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። 7 በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ። እነዚያም ሰዎች “እኛ በሰውነታችን ርኵሰት ያለብን ሰዎች ነን፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጊዜው ቍርባን ለእግዚአብሔር እንዳናቀርብ ስለ ምን እንከለከላለን?” አሉት። 8 ሙሴም፥ “እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ቈዩ” አላቸው። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ ወይም በተወለዳችሁበት ሀገር ያለም ቢሆን እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያድርግ። 11 በሁለተኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ያድርጉት፤ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 12 ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ፤ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዐት ሁሉ ያድርጉት። 13 ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ ፋሲካን ባያደርግ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ያ ሰው ኀጢአቱን ይሸከማል። 14 ወደ አገራችሁ መጻተኛ ቢመጣ፥ የእግዚአብሔርን ፋሲካ እንደ ፋሲካው ሕግ እንደ ትእዛዙም ያድርግ፤ ለመጻተኛና ለሀገር ልጅ አንድ ሥርዐት ይሁንላችሁ።” በእሳት አምሳል የታየው ደመና ድንኳኑን እንደ ጋረደው ( ዘፀ. 40፥34-38 ) 15 ድንኳንዋን በተከሉበት ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈናት፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በድንኳኑ ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር። 16 እንዲሁ ሁልጊዜ ነበረ፤ በቀን ደመና፥ በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍናት ነበር። 17 ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር። 18 በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፤ ደመናው በድንኳኑ ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር። 19 ደመናውም በድንኳኑ ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፤ አይጓዙምም ነበር። 20 ደመናው ድንኳኑን በጋረደበት ቀን ቍጥር ሁሉ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ቃል ይሰፍሩ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር። 21 አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። በቀንም በሌሊትም ቢሆን ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር 22 ደመናውም እስከ ወር ቈይቶ በድንኳኑ ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 23 በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፤ እግዚአብሔር በሙሴ ቃል እንደ አዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር። |