ነህምያ 3:1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ግንብ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ግንብ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሊቀ ካህኑ ኤልያሺብና ወንድሞቹ ካህናት ተነሥተው “የበግ በር” ሠሩ፤ ቀደሱት፥ በሩንም አቆሙ፤ እስከ “ሜአ ግንብ” እና እስከ “አሐናንኤል ግንብ” ድረስ ቀደሱት። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የከተማይቱ ቅጽር እንደገና የተሠራው በዚህ ዐይነት ነበር፦ ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብና የእርሱ ሥራ ባልደረቦች የሆኑት ካህናት “የበጎች በር” ተብሎ የሚጠራውን ቅጽር በር እንደገና ሠርተው ለእግዚአብሔር የተለየ አደረጉት፤ በሮችንም አበጁለት፤ ቅጽሩንም “መቶ” ተብሎ እስከሚጠራው የመጠበቂያ ግንብና “ሐናንኤል” ተብሎ እስከሚጠራው ሌላ የመጠበቂያ ግንብ ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ አደረጉት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ታላቁም ካህን ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ መቶ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ታላቁም ካህን ኤልያሴብ ወንድሞቹም ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፥ ቀደሱትም፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ እስከ ሃሜአ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት። |
ከዚያም ከኤፍሬም በር በላይ፣ በአሮጌ በር፣ በዓሣ በር፣ በሐናንኤል ግንብ፣ በመቶዎቹ ግንብ ዐልፌ እስከ በጎች በር ድረስ ተከተልኋቸው። እነርሱም በዘበኞች በር አጠገብ ሲደርሱ ቆሙ።
እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለበሮቹ መዝጊያ ባልገጥምላቸውም እንኳ፣ ቅጥሩን መሥራቴንና የቀረ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረባዊው ጌሳምና የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣
“ይህን ዕወቅ፤ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል። ኢየሩሳሌም ከጐዳናዎቿና ከቅጥሮቿ ጋራ ትታደሳለች፤ ይህ የሚሆነው ግን በመከራ ጊዜ ነው።
ምድር ሁሉ ከጌባዕ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሪሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።
በኢየሩሳሌም፣ በበጎች በር አጠገብ፣ ዐምስት ባለመጠለያ መመላለሻዎች የነበሯት፣ በአራማይክ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የተባለች አንዲት መጠመቂያ አለች።
አለቆቹም ለሰራዊቱ እንዲህ ይበሉ፤ “አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለን? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ቤቱን የሚያስመርቀው ሌላ ሰው ይሆናል።