Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ነህምያ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሥራው ቅንጅት

1 ሊቀ ካህኑ ኤልያሺብና ወንድሞቹ ካህናት ተነሥተው “የበግ በር” ሠሩ፤ ቀደሱት፥ በሩንም አቆሙ፤ እስከ “ሜአ ግንብ” እና እስከ “አሐናንኤል ግንብ” ድረስ ቀደሱት።

2 በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገቡም የኢምሪ ልጅ ዛኩር ሠራ።

3 የስናአ ልጆች “የዓሣ በር” ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ በሮቹን አቆሙ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም ሠሩ።

4 በአጠገባቸውም የቆጽ ልጅ የኡሪያ ልጅ ሜሬሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የመሼዛቤል ልጅ የቤሬክያ ልጅ ሜሹላም አደሰ። በአጠገባቸውም የባዓና ልጅ ጻዶቅ አደሰ።

5 በአጠገባቸውም ቴቁአውያን አደሱ፤ መኳንንቶቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አልሰጡም።

6 የፋሴሐ ልጅ ዮያዳ የቤሶዴያ ልጅ ሜሹላም “አሮጌ በር” አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ በሮቹንም አቆሙ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።

7 በአጠገባቸውም ጊብዖናዊው ሜላጥያ፥ ሜሮኖታዊው ያዶንና ከወንዙ ማዶ ያለው ገዢ ሥር የሆኑት የጊብዖንና የሚጽጳ ሰዎች አደሱ።

8 በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዚኤል አደሰ። በአጠገቡም የሽቶ ቀማሚዎች ልጅ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን አደሱ።

9 በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ ገዢ የሁር ልጅ ሬፋያ አደሰ።

10 በአጠገባቸውም የሐሩማፍ ልጅ ዬዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የሐሻቤኔያ ልጅ ሐጡሽ አደሰ።

11 የሐሪም ልጅ ማልኪያና የፓሐት ሞዓብ ልጅ ሐሹብ ሌላውን ክፍልና “የእቶን ግንብ” አደሱ።

12 በአጠገባቸውም እሱና ሴት ልጆቹ የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ ገዢ የሆነው የሃሎሔሽ ልጅ ሻሉም አደሰ።

13 ሐኑንና የዛኖሐ ሰዎችም “የሸለቆ በር” አደሱ፤ መልሰው ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አበጁ፤ ደግሞም እስከ “የፍግ በር” ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ።

14 የቤትሐካሪም አውራጃ ገዢ የሬካብ ልጅ ማልኪያ “የፍግ በር” አደሰ፤ መልሶ ሠራው፥ በሮቹን አቆመ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አበጀ።

15 የሚጽጳም አውራጃ ገዢ የኮልሖዜ ልጅ ሻሉን “የምንጭ በር” አደሰ፤ መልሶ ሠራው፥ ከደነውም፥ በሮቹን አቆመ፥ ቁልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አበጀ፤ በንጉሡ አትክልት ቦታ አጠገብ ያለውን የሼላሕን መዋኛ ቅጥር ከዳዊት ከተማ ወደ ታች እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ ሠራ።

16 ከእርሱም በኋላ የቤትጹር አውራጃ እኩሌታ ገዢ የሆነው የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር ፊት ለፊት እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራው መዋኛ ስፍራና እስከ ኃያላኑ ቤት ድረስ አደሰ።

17 ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሑም አደሱ። በአጠገቡ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዢ ሐሻብያ ስለ አውራጃው ብሎ አደሰ።

18 ከእርሱም በኋላ ወንድሞቻቸው፥ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዚ የሆነው የሔናዳድ ልጅ ባዋይ አደሱ።

19 በአጠገቡ የሚጽጳ ገዢ የኢያሱ ልጅ ዔዜር በግንቡ መደገፊያ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት መወጣጫ ፊት ለፊት ያለውን ሁለተኛውን ክፍል አደሰ።

20 ከእርሱም በኋላ የዛባይ ልጅ ባሮክ ሌላኛውን ክፍል ከግንቡ መደገፊያ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሺብ ቤት መግቢያ ድረስ በቀናኢነት አደሰ።

21 ከእርሱም በኋላ የቆጽ ልጅ የኡሪያ ልጅ ሜሬሞት ከኤልያሺብ ቤት በር ጀምሮ እስከ ኤልያሺብ ቤት መጨረሻ ድረስ ያለውን ክፍል አደሰ።

22 ከእርሱ በኋላ የአካባቢው ሰዎች ካህናቱ አደሱ።

23 ከእነርሱም በኋላ ብንያምና ሐሹብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የአናንያ ልጅ የማዓሤያ ልጅ አዛርያ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ።

24 ከእርሱም በኋላ የሔናዳድ ልጅ ቢኑይ ከዓዛርያ ቤት ጀምሮ እስከ የግንቡ መደገፊያ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።

25 የኡዛይ ልጅ ፓላል በግንቡ መደገፊያ ፊት ለፊት ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ፥ ከእርሱም በኋላ የፋኖስ ልጅ ፈዳያ ሠራ።

26 በዖፌል የተቀመጡ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች በምሥራቅ በኩል ካለው ከ “የውኃ በር” ፊት ለፊት ጀምሮ እስከ “የወጣው ግንብ” ድረስ አደሱ።

27 ከእርሱም በኋላ ቴቁአውያን ታላቁ “የወጣው ግንብ” ፊት ለፊት ጀምሮ እስከ “ዖፌል ቅጥር” ድረስ ያለውን ሌላውን ክፍል አደሱ።

28 ከ “የፈረሶች በር” በላይ ጀምሮ በየቤታቸው ትይዩ ያለውን ካህናቱ እያንዳንዳቸው አደሱ።

29 ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ጻዶቅ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን አደሰ። ከእርሱም በኋላ “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሼካኔያ ልጅ ሼማዔያ አደሰ።

30 ከእርሱ በኋላ የሼሌምያ ልጅ ሐናንያና የጻላፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኑን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከእርሱ በኋላ የቤሬክያ ልጅ ሜሹላም ከክፍሉ ፊት ለፊት ያለውን አደሰ።

31 ከእርሱም በኋላ የወርቅ አንጥረኛው ልጅ ማልኪያ ከ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ ቤት፥ የነጋዴዎቹ ቤት ጀምሮ እስከ “የመሰብሰቢያ በር” ፊት ለፊት ያለውንና እስከ ማዕዘኑ ላይኛው ክፍል ድረስ አደሰ።

32 ከማዕዘኑ ላይኛው ክፍል ጀምረው እስከ “የበግ በር” ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ።

33 ሳንባላጥ ቅጥሩን እየሠራን እንደሆነ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድ ላይም አፌዘ።

34 በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊት ፊት፦ “እነዚህ ደካሞች አይሁድ ምን እየሠሩ ነው? ለራሳቸው መልሰው እየገነቡ ነው? መሥዋዕትን ሊያቀርቡ ነው? በአንድ ቀንስ ይጨርሱታል? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ሊያድኑት ነው?” አለ።

35 አሞናዊው ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ ነበር፥ እንዲህም አለ፦ “የሚገነቡት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢወጣበት የድንጋይ ግንባቸውን ያፈርሰዋል፤”

36 አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው።

37 በደላቸውን አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ ሠራተኞችን በፊታቸው አስቆጥተዋቸዋልና።

38 ቅጥሩን ሠራን፤ የሕዝቡ ልብ ለሥራ ስለተነሣሣ ቅጥሩ ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos