ነህምያ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ታላቁም ካህን ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ መቶ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት። 2 በአጠገቡም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ የዘኩር ልጆች ሠሩ። 3 የአስናሃ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሠረገሎቹንም አኖሩ፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። 4 በአጠገባቸውም የቆስ ልጅ የኡርያ ልጅ ሚራሞት ይሠራ ጀመረ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ይሠራ ጀመረ። በአጠገባቸውም የበሃና ልጅ ሳዶቅ ይሠራ ጀመረ። 5 በአጠገባቸውም ቴቁሓውያን ይሠሩ ጀመሩ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለሥራው አንገታቸውን አላዋረዱም። 6 የፋሴሓ ልጅ ኢዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። 7 በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮናታዊው ያዴን፥ እስከ ወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የመሴፋ ሰዎች ሠሩ። 8 በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐሬህያ ልጅ ዑዝኤል ሠራ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ ሠራ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ። 9 በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ ሠራ። 10 በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን ሠራ። በአጠገቡም የአሰብንብሔም ልጅ ሐጡስ ሠራ። 11 የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኑን ግንብ ሠሩ። 12 በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ ገዢ የአሎኤስ ልጅ ሰሎምና ሴቶች ልጆቹ ሠሩ። 13 ሐኖንና የዘናን ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያ በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ። 14 የቤትሐካሪምም ግዛት ገዢ የሬካብ ልጅ መልክያ ከወንድሞቹና ከልጆቹ ጋር የጕድፍ መጣያውን በር ሠራ፤ ከደነው፤ ሳንቃዎቹንም አቆመ፤ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ። 15 የመሴፋም ገዢ የኮልሐዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፤ ከደነውም፤ ሳንቃዎቹንም አቆመ፤ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የመዋኛ ቅጥር ሠራ። 16 ከእርሱም በኋላ የቤሶር ግዛት እኩሌታ ገዢ የዓዛቡህ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኀያላኑም ቤት ድረስ ሠራ። 17 ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም ሠሩ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኩሌታና የአውራጃዎችዋ ገዢ አሰብያ ሠራ። 18 ከእርሱም በኋላ የቅዔላ ግዛት እኩሌታ ገዢ የኤንሐዳድ ልጅ ቤኒይና ወንድሞቹ ሠሩ። 19 በአጠገቡም የመሴፋ ገዢ የኢያሱ ልጅ አዙር በማዕዘኑ አጠገብ በመወጣጫው ግንብ አንጻር ያለውን ሌላውን ክፍል ሠራ። 20 ከእርሱም በኋላ የዘቡር ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ ሠራ። 21 ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኡርያ ልጅ ሚራሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እሰከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል ሠራ። 22 ከእርሱም በኋላ የአካባቢው ሰዎች ካህናቱ ሠሩ። 23 ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሴብ በቤታቸው አንጻር ያለውን ሠሩ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዓስያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን ሠራ። 24 ከእርሱም በኋላ የኢንሓዳድ ልጅ ባኒ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ እስከ ግንቡመዞሪያ ድረስ ያለውን ሌላውን ክፍል ሠራ። 25 የኡዛይ ልጅ ፋልል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ። 26 ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ። 27 ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል ሠሩ። 28 ከፈረሶች በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር ሠሩ። 29 ከዚያም በኋላ የሄሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር ያለውን ሠራ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁ በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሰማያ ሠራ። 30 ከእርሱም በኋላ የሰሎምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል ሠሩ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በሙዳየ ምጽዋቱ አንጻር ያለውን ሠራ። 31 ከእርሱም በኋላ የሰራፊ ልጅ መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሜፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ ሠራ። 32 ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጎች በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች ሠሩ። |