ናሆም 1:3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ለቁጣ የዘገየ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ ንጹሕ ነህ አይልም፤ ጌታ መንገዱ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ነው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ታጋሽና ኀያል ነው፤ ነገር ግን በደለኛውን ሳይቀጣው አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በሞገድ ውስጥ ነው፤ ሰው ሲራመድ ትቢያን እንደሚያስነሣ፥ የእግዚአብሔርም መገለጥ ደመናን ያስከትላል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ ንጹሕ ነህ አይልም፣ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። |
ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤
ስለ ግብጽ የተነገረ ንግር፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጻውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በነጐድጓድ፣ በምድር መናወጥና በታላቅ ድምፅ፣ በዐውሎ ነፋስና በኀይለኛ ሞገድ፣ ፈጽሞ በሚባላም የእሳት ነበልባል ይመጣል።
እነሆ፤ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ይመጣል፤ ሠረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ ንዴቱን በቍጣ፣ ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይገልጣል።
ልባችሁን እንጂ፣ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣ ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና።
ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁትስ ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የተነሣሁትም ለዚሁ ነበር፤ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣ የዘገየህ አምላክ፣ ምሕረትህ የበዛ፣ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ።
እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ይገለጣል፤ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔር መለከት ይነፋል፤ በደቡብም ዐውሎ ንፋስ ውስጥ ይጓዛል፤
‘እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’
ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው።
“እነሆ፤ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሳይቀሩ፣ ዐይን ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከርሱ የተነሣ ዋይ ዋይ ይላሉ።” አዎ! ይህ ሁሉ ይሆናል። አሜን።