ኤርምያስ 30:3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል ጌታ፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይወርሱአታል፥ ይላል ጌታ።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን እንደገና የምመልስበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም እንደገና የራሳቸው ያደርጓታል። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነሆ! የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይገዙአታል።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይገዙአታል። |
የቀድሞውን ቤተ መቅደስ ያዩ በዕድሜ የሸመገሉ ብዙ ካህናት፣ ሌዋውያንና የቤተ ሰብ አለቆች የዚህ ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል ባዩ ጊዜ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ሌሎቹ ግን የደስታ ጩኸት አሰሙ።
ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር፣ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ እንዲሁም የቀሩት ወንድሞቻቸው (ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሁሉ) ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤት ሕንጻ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ሾሟቸው፤ ሥራውንም ጀመሩ።
ምነው ለእስራኤል የሚሆን መዳን ከጽዮን በወጣ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በሚመልስበት ጊዜ፣ ያዕቆብ ደስ ይበለው፤ እስራኤልም ሐሤት ያድርግ።
“ነገር ግን፣ ‘እስራኤላውያንን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ይላሉ፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁና።
“እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር።
ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዐንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ማንኛውንም ሕዝብ በገዛ ምድሩ እንዲቀርና እያረሰም በዚያ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።” ’ ”
‘ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤ እስከምጐበኛቸውም ቀን ድረስ በዚያ ይቀመጣሉ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘በዚያ ጊዜም እመልሳቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’ ”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።
እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”
“ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤ እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘አንተን ከሩቅ አገር፣ ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤ ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤ የሚያስፈራውም አይኖርም።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጕብታ ላይ ትሠራለች፤ ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ድምፅሽን ከልቅሶ፣ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤” ይላል እግዚአብሔር። “ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኳቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ።
‘በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ ያለ ሥጋትም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።
ምርኳቸውን ስለምመልስላቸው በብንያም አገር፣ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች፣ በይሁዳ ከተሞችና በተራራማው አገር ከተሞች፣ በምዕራብ ተራሮች ግርጌና በኔጌብ ባሉ ከተሞች፣ መሬት በጥሬ ብር ይገዛል፤ ውሉም ተፈርሞ፤ በምስክሮች ፊት ይታሸጋል፤’ ይላል እግዚአብሔር።”
የያዕቆብንና የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፤ ከልጆቹም በአብርሃም፣ በይሥሐቅና በያዕቆብ ዘር ላይ ገዥ እንዲሆኑ አልመርጥም፤ ይህንም የምለው ምርኳቸውን ስለምመልስና ስለምራራላቸው ነው።’ ”
ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።
ይህም ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሰጣል፤ እነርሱም በዚያ መሰማሪያ ያገኛሉ። በአስቀሎና ቤቶች ውስጥም በምሽት ይተኛሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋል፤ ምርኳቸውንም ይመልስላቸዋል።
በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።
ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል፤ “ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ፣ አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ።