ዘፍጥረት 43:8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋራ ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፣ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፥ አንተም፥ እኛም፥ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይሁዳም አባቱን እንዲህ አለ፤ “ልጁን በእኔ ኀላፊነት አብሮን እንዲሄድ አድርግ፥ ሳንዘገይ አሁኑኑ ጒዞ እንጀምር፤ ይህ ከሆነ፥ እኛም አንተም ልጆቻችንም ሁሉ በራብ ከመሞት እንድናለን። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው፥ “እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን፥ እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ላከው፤ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው፦ እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው እናም ተንሥተን እንሄዳለን። |
ያዕቆብም፣ “ልጄ ዐብሯችሁ ወደዚያ አይወርድም፤ ወንድሙ እንደሆን ሞቷል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው። ይዛችሁት ስትሄዱ በመንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበት፣ ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ” አላቸው።
እኛም፣ ‘አዎን፣ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቷል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወድደዋል’ ብለንህ ነበር።
‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ዐብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በቀር፣ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው።
“ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብጽ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጕዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ።
እንደዚሁም የዮሴፍ ቤተ ሰዎች፣ ወንድሞቹና ሌሎችም የአባቱ ቤተ ሰዎች በሙሉ ዐብረውት ሄዱ። በጌሤም የቀሩት ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋዎቻቸው ብቻ ነበሩ።
ከጦር አለቆቹም አንዱ እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ሰዎች በከተማዪቱ ውስጥ ከተረፉት ፈረሶች ዐምስቱን ይዘው ይሂዱ፤ ዕጣ ፈንታቸውም በዚህ ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ዕድል ጋራ አንድ ነው፤ የሚጠብቃቸው ቢኖር በዚህ በሙሉ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ብቻ ነው፤ ስለዚህ እንላካቸውና የሆነውን እንይ።”
ታዲያ፣ ‘ወደ ከተማዪቱ እንግባ ብንል’ በዚያም ራብ ስላለ እንሞታለን፤ በዚሁም ብንሆን ያው መሞታችን አይቀርም፤ ስለዚህ ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር ዝም ብለን እንሂድ፤ ዝም ካሉን ሕይወታችን ትተርፋለች፤ ከገደሉንም ሞቶ መገላገል ነው።”
ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጕዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።