ዘፍጥረት 43 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዮሴፍ ወንድሞች ከብንያም ጋር ወደ ግብፅ እንደ ሄዱ 1 ከዚህም በኋላ ራብ በሀገር ላይ ጸና። 2 ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው፥ “እንደገና ሂዱ፤ ጥቂት እህል ሸምታችሁ አምጡልን” አላቸው። 3 ይሁዳም እንዲህ አለው፥ “የሀገሩ ጌታ ያ ሰው፦ ‘ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ከአልመጣ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በምስክር ፊት አዳኝቶብናል። 4 ወንድማችንን ከእኛ ጋር ብትልከው እንወርዳለን፤ እህልም እንሸምትልሃልን፤ 5 ወንድማችንን ከእኛ ጋር ባትልከው ግን አንሄድም፤ ያ ሰው ‘ታናሽ ወንድማችሁን ከእናንተ ጋር ካላመጣችሁ ፊቴን አታዩም’ ብሎናልና።” 6 እስራኤልም አላቸው፥ “በእኔ ላይ ያደረጋችኋት ይህች ክፋት ምንድን ናት? በዚያውስ ላይ ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለምን ነገራችሁት?” 7 እነርሱም አሉ፥ “ያ ሰው ስለ እኛና ስለ ትውልዳችን ፈጽሞ ጠየቀን፤ እንዲህም አለን፦ ‘ሽማግሌው አባታችሁ ገና በሕይወት ነው? ወንድምስ አላችሁን?’ እኛም እንደዚሁ እንደ ጠየቀን መለስንለት፤ በውኑ፦ ‘ወንድማችሁን አምጡ’ እንዲለን እናውቅ ነበርን?” 8 ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው፥ “እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን፥ እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ላከው፤ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን። 9 እኔ እዋሳለሁ፤ ከእጄ ትሻዋለህ፤ ወደ አንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁህ ልሁን። 10 ባንዘገይስ ኖሮ አሁን ሁለተኛ ጊዜ በተመለስን ነበር።” 11 አባታቸው እስራኤልም እንዲህ አላቸው፥ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ ፤ ከምድሩ ፍሬ በዓይበታችሁ ይዛችሁ ሂዱ፤ ለዚያም ሰው እጅ መንሻ፥ ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ዕጣን፥ ተምር፥ ለውዝ ውሰዱ። 12 ብሩን በአጠፌታ አድርጋችሁ በእጃችሁ ውሰዱ፤ በዓይበታችሁም አፍ የተመለሰውን ብር መልሳችሁ ውሰዱ፤ ምናልባት ባለማወቅ ይሆናል። 13 ወንድማችሁንም ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤ ተነሥታችሁም ወደዚያ ሰው ውረዱ። 14 አምላኬም በዚያ ሰው ፊት ሞገስን ይስጣችሁ፤ ያን ወንድማችሁንና ብንያምንም ይመልስላችሁ፤ እኔም ልጆችን እንዳጣሁ አጣሁ።” 15 ሰዎቹም በእጃቸው ያችን እጅ መንሻና ብራቸውን በእጥፍ፥ ብንያምንም ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዮሴፍም ፊት ቆሙ፤ ሰገዱለትም። 16 ዮሴፍም ብንያምን ከእነርሱ ጋር በአየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “እነዚያን ሰዎች ወደ ቤት አስገባቸው፤ እርድም እረድ፤ አዘጋጅም፤ እነዚያ ሰዎች በእኩለ ቀን ከእኔ ጋር ይበላሉና።” 17 ያም ሰው ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባ። 18 እነዚያም ሰዎች ወደ ዮሴፍ ቤት እንደ ገቡ በአዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፥ “በዓይበታችን ቀድሞ ስለ ተመለሰው ብር ሊተነኰሉብን፥ ሊወድቁብንም፥ እኛንም በባርነት ሊገዙን፥ አህዮቻችንንም ሊወስዱ ወደዚህ አስገቡን።” 19 ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥም ቀረቡ፤ በቤቱም ደጅ ተናገሩት፤ 20 እንዲህም አሉ፥ “ጌታ ሆይ፥ እንማልድሃለን፤ ቀድሞ እህልን ልንሸምት ወርደን ነበር፤ 21 እንዲህም ሆነ፥ ወደምናድርበትም ስፍራ በደረስን ጊዜ ዓይበታችንን ከፈትን፤ እነሆም፥ የየአንዳንዱ ሰው ብር በየዓይበቱ አፍ ነበር፤ አሁንም ብራችንን በእጃችን እንደ ሚዛኑ መለስነው። 22 እህል እንሸምትበት ዘንድ ሌላም ብር በእጃችን አመጣን፤ ብራችንንም በዓይበታችን ማን እንደ ጨመረው አናውቅም።” 23 እርሱም አላቸው፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ አትፍሩ፤ አምላካችሁ የአባቶቻችሁ አምላክ በዓይበታችሁ የተሰወረ ገንዘብ ሰጣችሁ፤ ብራችሁንስ መዝኜ ተቀብያለሁ።” 24 ስምዖንንም ወደ እነርሱ አወጣላቸው። እግራቸውንም ሊታጠቡ ውኃ አመጣላቸው፤ ለአህዮቻቸውም ገፈራ ሰጣቸው። 25 ዮሴፍም በእኩለ ቀን እስኪገባ ድረስ እነርሱ እጅ መንሻቸውን አዘጋጁ፤ ከዚያ ምሳ እንደሚበሉ ሰምተዋልና። 26 ዮሴፍም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በእጃቸው ያለውን እጅ መንሻ በቤት ውስጥ አቀረቡለት፤ ወደ ምድርም በግንባራቸው ወድቀው ሰገዱለት። 27 እርሱም ደኅንነታቸውን ጠየቃቸው፤ እንዲህም አለ፥ “የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን? ገና በሕይወት አለን?” 28 እነርሱም አሉት፥ “ባሪያህ ሽማግሌው አባታችን ደኅና ነው፤ ገና በሕይወት አለ።” ዮሴፍም አለ፥ “ሰውየው እግዚአብሔር የባረከው ነው።” ራሳቸውንም ዝቅ አድርገው ሰገዱለት። 29 ዮሴፍም ዐይኑን አንሥቶ የእናቱን ልጅ ወንድሙ ብንያምን አየው፤ እርሱም አለ፥ “ወደ አንተ እናመጣዋለን ብላችሁ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነውን?” እነርሱም፥ “አዎን” አሉት። እንዲህም አለው፥ “ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ።” 30 ዮሴፍም ታወከ፤ አንጀቱ ወንድሙን ናፍቆታልና፤ ሊያለቅስም ወደደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ በዚያ አለቀሰ። 31 ፊቱንም ታጥቦ ተጽናንቶም ወጣ። “እንጀራ አቅርቡልን” አለ። 32 ለእርሱም ለብቻው አቀረቡ፤ ለእነርሱም ለብቻቸው፤ ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ለግብፅ ሰዎችም ለብቻቸው፤ የግብፅ ሰዎች ከዕብራውያን ጋር መብላት አይችሉምና፥ ይህ ለግብፅ ሰዎች እንደ መርከስ ነውና። 33 በፊቱም በኵሩ እንደ ታላቅነቱ፥ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ ተቀመጡ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው በመደነቅ ተያዩ። 34 በፊቱም ከአለው መብል ፈንታቸውን አቀረበላቸው፤ የብንያምም ፈንታ ከሁሉ አምስት እጅ የሚበልጥ ነበረ። እነርሱም በሉ፤ ጠጡም፤ ከእርሱም ጋር ደስ አላቸው። |