ዘፍጥረት 33:4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዔሳውም ሊገናኘው ሮጦ ተጠመጠመበት፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፥ ተላቀሱም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጠ፤ በአንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ዕቅፍ አድርጎ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ፤ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፤ ሁለቱም በአንድነት አለቀሱ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ አንገቱንም አቅፎ ሳመው ተላቀሱም። |
ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው።
ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፣ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ ዐምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ ዐብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ።
ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደ ደረሰ፣ ዐንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ለረዥም ጊዜ አለቀሰ።
ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ይህንኑ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
ጌታ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎት፣ ስምህን በመፍራት ደስ የሚሰኙትን የባሪያዎችህንም ጸሎት ጆሮህ ታድምጥ። በዚህ ሰው ፊት ሞገስን አድርገህለት ዛሬ ለባሪያህ መከናወንን ስጠው።” በዚያ ጊዜ እኔ የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበርሁ።
እነርሱም ከሩቅ ሆነው ሲመለከቱት እርሱ መሆኑን ሊለዩ አልቻሉም፤ በዚህ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ልብሳቸውንም ቀድደው በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ።
ልጁ ከሄደ በኋላ፣ ዳዊት ከድንጋዩ በስተ ደቡብ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ በዮናታን ፊት ሦስት ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደለት፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱም፤ በይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር።