ዘፍጥረት 33 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ያዕቆብ ከዔሳው ጋር መገናኘቱ 1 ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ ተመለከተም፥ እነሆም ዔሳው እየመጣ ነበር፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ። ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም አገልጋዮች አደረጋቸው። 2 ሴት አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውንም ከፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም አስከተለ፥ ከዚያም ራሔልንና ዮሴፍን ከሁሉ በኋላ አደረገ። 3 እርሱም ከፊታቸው ቀደመ፥ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ። 4 ዔሳውም ሊገናኘው ሮጦ ተጠመጠመበት፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፥ ተላቀሱም። 5 ዓይኑን አንስቶም ሴቶችንና ልጆችን ባየ ጊዜ፥ “እነዚህ ምኖችህ ናቸው?” አለ። እርሱም፦ “እግዚአብሔር ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለ። 6 ከዚህ በኋላ ሴቶች ባርያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው እጅ ነሡ፥ 7 ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀረበው እጅ ነሡ፥ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል ቀርበው እጅ ነሡ። 8 እርሱም፥ “ያገኘሁት ይህ ሁሉ ጓዝ ምንህ ነው?” አለ። እርሱም፥ “በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ነው” አለ። 9 ዔሳውም፥ “ለእኔ ብዙ አለኝ፥ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን አለ።” 10 ያዕቆብም አለ፥ “እንደዚህ አይሁን፥ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆንሁ፥ እጅ መንሻዬን ተቀበለኝ፥ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና። 11 ይህንም ያመጣሁልህን ስጦታዬን ተቀበል፥ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ጎብኝቶኛልና፥ ለእኔም በቂ አለኝና።” በዚህም መልክ ግድ አለው፥ እርሱም ተቀበለው። ያዕቆብ ከዔሳው ተለየ 12 እርሱም ተነሣና “እንግዲህ እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ” አለ። 13 እርሱም አለው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፥ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ መጠንቀቅ ይኖርብኛል፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደሆነ እንሰሶቹ ሁሉ ይሞታሉ። 14 እባክህ ጌታዬ ከአገልጋዩ ፊት ቀድሞ ይለፍ፥ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በልጆቹ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።” 15 ዔሳውም፥ “ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን” አለ። እርሱ ግን፥ “ይህ ለምንድን ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘት ይበቃኛል” አለ። 16 ዔሳውም በዚያኑ ቀን ወደ ሴይር መንገዱ ተመለሰ። 17 ያዕቆብ ግን ወደ “ሱኮት” ሄደ፥ ከዚያም ለራሱ ቤትን ሠራ፥ ለከብቶቹም ዳሶችን አደረገ። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም “ሱኮት” ብሎ ጠራው። ያዕቆብ ሴኬም መድረስ 18 ያዕቆብም፥ ከፓዳን-ኣሪም በተመለሰ ጊዜ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው፥ ሴኬም ከተማ በሰላም መጣ፥ እናም በከተማይቱ ፊት ለፊት ሰፈረ። 19 ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የመስክ ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው። 20 እዚያም መሠውያውን አቆመ፥ ያንም ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው። |