Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


መዝሙር 34 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 34
እንደ እብድ ሆኖ አቢሜሌክ ፊት በመቅረቡ ተባርሮ በወጣ ጊዜ የዘመረው፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም።

2 ነፍሴ በእግዚአብሔር ተመካች፤ ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ።

3 ኑና ከእኔ ጋራ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።

4 እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።

5 ወደ እርሱ የሚመለከቱ ያበራሉ፤ ፊታቸውም ከቶ አያፍርም።

6 ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው።

7 እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም።

8 እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ብፁዕ ነው!

9 እናንተ ቅዱሳኑ፤ እግዚአብሔርን ፍሩት፤ እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።

10 አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም።

11 ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።

12 ሕይወትን የሚወድድ፣ በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው?

13 አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤ ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ።

14 ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤ ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም።

15 የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።

16 የእግዚአብሔር ፊት ግን፣ መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።

17 ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል።

18 እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።

19 የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል።

20 ዐጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።

21 ኀጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል፤ ጻድቃንን የሚጠሉ ይፈረድባቸዋል።

22 እግዚአብሔር የባሪያዎቹን ነፍስ ይቤዣል፤ እርሱንም መጠጊያ ያደረገ አይፈረድበትም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos