2 ሳሙኤል 21:1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፣ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም፥ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፥ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በዳዊት ዘመነ መንግሥት ሦስት ዓመት ሙሉ ጽኑ ራብ ነበር፤ ዳዊትም ስለዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር “ሳኦልና ቤተሰቡ ግድያ በመፈጸም በደል ሠርተዋል፤ ሳኦልም የገባዖንን ሰዎች ፈጅቶአል” ሲል መለሰለት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል በተከታታይ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ቃል ጠየቀ። እግዚአብሔርም አለ፥ “የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት፥” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ቀጥሎ ራብ ሆነ፥ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። |
መንግሥቱን የወሰድህበትን የሳኦልን ቤተ ሰው ደም ሁሉ እግዚአብሔር ወደ አንተው እየመለሰው ነው። እግዚአብሔር መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አንተ የደም ሰው ስለ ሆንህ እነሆ፣ መከራ መጥቶብሃል።”
ስለዚህም ዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ ወጥቼ ልምታቸውን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ሂድ፤ በርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።
ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤
በዚህ ጊዜ ከገለዓድ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፣ “በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” አለው።
ከተማዪቱን እንደ ከበባትም የአንድ አህያ ጭንቅላት በሰማንያ ሰቅል ብር፣ የጎሞር አንድ ስምንተኛ የርግብ ኵስ በዐምስት ሰቅል ብር እስኪሸጥ ድረስ ታላቅ ራብ ሆነ።
በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ፣ ልጇ ከሞት ያስነሣላትን ሴት፣ “እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የሰባት ዓመት ራብ ስለ ወሰነ፣ ተነሺና ለጊዜው መቈየት ወደምትችዪበት ቦታ ከቤተ ሰብሽ ጋራ ሂጂ” አላት።
የእንጀራችሁ እህል እንዲቋረጥ በማደርግበት ጊዜ፣ ዐሥር ሴቶች በአንድ ምጣድ ላይ እንጀራ ይጋግራሉ፤ እንጀራውንም በሚዛን መዝነው እናንተም ትበላላችሁ፤ ግን አትጠግቡም።
እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሆኖ በኡሪም በመጠየቅ ውሳኔ በሚያስገኝለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል፤ እርሱም ሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በአልዓዛር ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በርሱም ቃል ይገባሉ።”
እስራኤላውያን ግን ዕርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ ዕርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።
መሳፍንት በሚገዙበት ዘመን፣ በምድሪቱ ላይ ራብ ሆነ፤ አንድ ሰው በይሁዳ ከምትገኘው ከቤተ ልሔም ሚስቱንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ለመኖር ወደ ሞዓብ አገር ሄደ።
የቅዒላ ገዦች አሳልፈው ይሰጡኝ ይሆን? ባሪያህ እንደሰማውም ሳኦል ወደዚህ ይወርድ ይሆን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ እንድትነግረው እለምንሃለሁ።” እግዚአብሔርም፣ “አዎን ይወርዳል” አለው።
እርሱም፣ “እነዚህን ፍልስጥኤማውያን ሄጄ ልምታን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “ሂድ፤ ፍልስጥኤማውያንን ምታ፤ ቅዒላንም አድናት” ብሎ መለሰለት።