2 ሳሙኤል 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሳኦል ዘሮች በሞት እንደ ተቀጡ 1 በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል በተከታታይ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ቃል ጠየቀ። እግዚአብሔርም አለ፥ “የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት፥” 2 ንጉሡ ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፤ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። 3 ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች፥ “የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስረያውስ ምንድን ነው?” አላቸው። 4 የገባዖን ሰዎችም፥ “ከሳኦልና ከቤቱ ወርቅ ወይም ብር አንፈልግም፤ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም” አሉት። 5 እርሱም፥ “ምን ትላላችሁ? ተናገሩ፤ እኔም አደርግላችኋለሁ” አላቸው፤ እነርሱም ለንጉሡ አሉት፥ “በእኛ ላይ ክፉ ያደረገውን፥ ያሳደደንንና ሊያጠፋን ያሰበውን ሰው እናጥፋው፤ እርሱም በእስራኤል ዳርቻ እንዳይቆም እናደርገዋለን። 6 ከልጆቹ ሰባት ሰዎች ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል ሀገር በገባዖን ለእግዚአብሔር እንሠቅላቸዋለን።” ንጉሡም፥ “እሰጣችኋለሁ” አለ። 7 ንጉሡም በእነርሱ መካከል፥ በዳዊትና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፌቡስቴን ራራለት። 8 ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄልን ልጅ የሩጻፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንስቴንና ሜምፌቡስቴን፥ ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድራ የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፤ 9 በገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ እህል በሚታጨድበትም ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ። 10 የኢዮሔል ልጅ ሩጻፋም ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው፤ በቀንም የሰማይ ወፎች፥ በሌሊትም የዱር አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። 11 የሳኦልም ዕቅብት የኢዮሔል ልጅ ሩጻፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። 12 ዳዊትም ሄደ፤ ሳአልንም በጌላቡሄ በገደሉት ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቤስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልን አጥንትና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ። 13 ከዚያም የሳኦልን አጥንትና የልጁን የዮናታንን አጥንት አመጣ፤ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። 14 የሳኦልን አጥንትና የልጁን የዮናታንን አጥንት፥ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት በብንያም በአባቱ በቂስ መቃብር አጠገብ ቀበሩአቸው፤ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ምድርን ሰማት። በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል የተደረገ ጦርነት ( 1ዜ.መ. 20፥4-8 ) 15 በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤልም መካከል ደግሞ ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም፥ ከእርሱም ጋር አገልጋዮቹ ወረዱ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ ዳዊትም ደከመ። 16 ከራፋይም ወገን የነበረው ኤስቢ መጣ፤ የጦሩም ሚዛን ክብደት ሦስት መቶ ሰቅል ናስ ነበር። አዲስ የጦር መሣሪያም ታጥቆ ነበር፤ ዳዊትንም ሊገድለው ፈለገ። 17 የሶርህያም ልጅ አቢሳ አዳነው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ወግቶ ገደለው። ያንጊዜም የዳዊት ሰዎች፥ “አንተ የእስራኤል መብራት እንዳትጠፋ ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ለሰልፍ አትወጣም” ብለው ማሉለት። 18 ከዚህም በኋላ እንደ ገና በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ሆነ፤ ያን ጊዜም አስጣጦታዊው ሴቤኮይ ከራፋይም ወገን የሆነውን ሳፍን ገደለው። 19 ደግሞም በሮም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ሆነ፤ የቤተልሔማዊውም የዓሬኦርጌም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው ጎዶልያን ገደለው። 20 ደግሞም በጌት ላይ ጦርነት ሆነ፤ በዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስትሁላሁሉ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረዥም ሰው ነበረ፤ እርሱ ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። 21 እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሴማይ ልጅ ዮናታን ገደለው። 22 እነዚያም አራቱ በጌት ውስጥ ከረዐይት የተወለዱ የራፋይም ወገኖች ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በአገልጋዮቹም እጅ ወደቁ። |