Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ነገሥት 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሱነማዪቱ ርስት ተመለሰ

1 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ፣ ልጇ ከሞት ያስነሣላትን ሴት፣ “እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የሰባት ዓመት ራብ ስለ ወሰነ፣ ተነሺና ለጊዜው መቈየት ወደምትችዪበት ቦታ ከቤተ ሰብሽ ጋራ ሂጂ” አላት።

2 ሴቲቱም ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገራት አደረገች፤ ከነቤተ ሰቧም ሄዳ፣ በፍልስጥኤም ምድር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።

3 ከሰባት ዓመት በኋላም፣ ከፍልስጥኤም ምድር ተመልሳ መጣች፤ ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ አቤቱታ ለማቅረብም ወደ ንጉሡ ሄደች።

4 በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው አገልጋይ ግያዝን፣ “ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እስኪ ንገረኝ” እያለው ነበር።

5 ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሣላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለማመልከት ወደ ንጉሡ ዘንድ የቀረበችውም፣ ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሣ ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ወቅት ነበር። ግያዝም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጇም ይህ ነው” አለ።

6 ንጉሡም ስለ ስለዚሁ ጕዳይ ጠየቃትና ነገረችው። ከዚያም ንጉሡ፣ “የነበራትን ሁሉ እንዲሁም ትታ ከሄደችበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የዕርሻዋን ሰብል በሙሉ እንድትመልስላት” ሲል አንድ ሹም አዘዘላት።


አዛሄል ቤን ሃዳድን ገደለ

7 ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በዚያ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሃዳድ ታምሞ ነበር፤ ለንጉሡም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቷል” ብለው ነገሩት።

8 ንጉሡም አዛሄልን፣ “ገጸ በረከት ይዘህ ሂድና የእግዚአብሔርን ሰው ተገናኘው። በርሱም አማካይነት፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው።

9 አዛሄልም ደማስቆ ካፈራቻቸው ምርጥ ነገሮች ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ይዞ ኤልሳዕን ለመገናኘት ሄደ። ሄዶም ፊቱ ቆመና፣ “የሶርያ ንጉሥ ልጅህ ቤን ሃዳድ፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ሲል ወደ አንተ ልኮኛል” አለው።

10 ኤልሳዕም፣ “ሂድና፣ ‘መዳኑንስ በርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጾልኛል” ሲል መለሰለት።

11 እስኪያፍር ድረስም፣ አዛሄልን ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው እንባውን አፈሰሰ።

12 አዛሄልም፣ “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። ኤልሳዕም መልሶ፣ “በእስራኤላውያን ላይ የምታደርሰውን ጕዳት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጕልማሶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናታቸውን በምድር ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ ያረገዙ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ” አለው።

13 አዛሄልም፣ “ለመሆኑ እንደ ውሻ የሚቈጠር አገልጋይህ ይህን ጀብዱ መፈጸም እንዴት ይችላል?” አለ። ኤልሳዕም መልሶ፣ “መቼም አንተ በሶርያ ላይ እንደምትነግሥ እግዚአብሔር አሳይቶኛል” አለው።

14 ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤን ሃዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው።

15 በማግስቱም ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።


የይሁዳ ንጉሥ ይሆራም
8፥17-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 21፥5-10 ፤ 21፥20

16 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ይሆራም በይሁዳ ነገሠ።

17 እርሱ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

18 እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

19 ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም መብራት እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

20 በይሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።

21 ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ተሻገረ። በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ሁሉ የከበቧቸውን ኤዶማውያንን መታ፤ ሰራዊቱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።

22 ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐምፆ ነበር።

23 በኢዮራም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

24 ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እንደ እነርሱም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስም በምትኩ ነገሠ።


የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ
8፥25-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥1-6

25 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ በይሁዳ ነገሠ።

26 አካዝያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ጎቶልያ ትባላለች። እርሷም የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች።

27 አካዝያስ ከአክዓብ ቤተ ሰብ ጋራ በጋብቻ የተሳሰረ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

28 አካዝያስም ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋራ ሆኖ በሶርያ ንጉሥ በአዛሄል ላይ ለመዝመት ወደ ራሞት ገለዓድ ሄደ፤ ሶርያውያንም በዚያ ኢዮራምን አቈሰሉት።

29 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፣ ከአዛሄል ጋራ ራማት ላይ ባደረገው ጦርነት ሶርያውያን ካቈሰሉት ቍስል ለመዳን ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። ከዚያም የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ስለ ታመመ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራሆም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos