ራእይ 2:2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሥራህን፥ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ክፉዎችን ግን ልትታገሣቸው እንዳልቻልክ፥ ሐዋርያት ሳይሆኑም ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሥራህን፣ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ። ክፉዎችንም ችላ ብለህ እንዳላለፍሃቸው፣ ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትንም መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንደማትችል፥ እንዲሁም ሐዋርያት ሳይሆኑ ‘ነን’ የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ ‘ሐዋርያት ነን’ የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ |
ይህንንም ያልኩት ግራ የሚያጋቡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ስላሉ ነው እንጂ ወንጌልማ በመሠረቱ አንድ ብቻ ነው።
ከእንግዲህ ወዲህ በሰዎች የተንኰል ሽንገላና አታላይነት በተዘጋጀ በአሳሳች የትምህርት ነፋስና ሞገድ ወዲያና ወዲህ ተገፍትረው እንደሚወሰዱ ሕፃናት አንሆንም።
በአምላካችንና በአባታችን ፊት እምነታችሁ የሚሠራውን፥ ለፍቅር የምታደርጉትንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቃችሁን ሳናቋርጥ እናስታውሳለን።
ነገር ግን “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይኖራል።
ወዳጆች ሆይ! በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ስለ ተነሡ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ይልቅስ መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሩ።
ከምን ያኽል ከፍተኛ ቦታ ላይ መውደቅህን አስታውስ! ንስሓም ግባ! በመጀመሪያ ታደርገው የነበረውን ሥራህን አድርግ፤ ይህን ሁሉ ባታደርግ ግን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ንስሓም ካልገባህ መቅረዝህን ከስፍራው አነሣዋለሁ።
መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ፥ የሰይጣን ማኅበር የሆኑ፥ ስምህን እንዳጠፉት ዐውቃለሁ፤
“ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ ሰባቱን የእግዚአብሔር መንፈሶችና ሰባቱን ኮከቦች ከያዘው የተነገረ ነው፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል።
ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም ሊዘጋው የማይችለውን የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌልሃለሁ፤ ኀይልህ ትንሽ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም።