ማርቆስ 4:19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብ፥ የሀብት ፍቅርና ሌላውም ከንቱ ምኞት ወደ ልባቸው ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፤ የማያፈራም ይሆናል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፤ የማያፈራም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። |
እነሆ፥ ብቻውን የሚኖር አንድ ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁን እንጂ ዘወትር በሥራ ከመድከም አይቦዝንም፤ ባገኘውም ሀብት በቃኝ ማለትን አላወቀም፤ “እርሱም የምደክመው ለማን ነው? ለራሴስ ደስታን የምነፍገው ለምንድን ነው?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል፤ ይህ ሁሉ የባሰ ከንቱና የሥቃይ ሕይወት ነው።
መሬቱን በመቈፈርና ድንጋዩንም ለቅሞ በማውጣት ምርጥ የሆነውን የወይን ሐረግ ተከለበት፤ በመካከሉም መጠበቂያ የሚሆን ማማ ሠራለት፤ ጒድጓድ ቆፍሮም የወይን ፍሬ መጭመቂያ አበጀለት። ከዚያን በኋላ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ጠበቀ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ።
ለመሆኑ እኔ ለእርሱ ያላደረግኹለት ነገር አለን? ከዚህስ ሌላ ላደርግለት የሚገባ ምን አለ? ታዲያ፥ መልካም ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቀው ስለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ?
በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል።
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ለሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት በጣም ከባድ ነው።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ! አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይይዛችኋል።
በእኔ ላይ ያለውን ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ አባቴ ቈርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ግን አብዝቶ እንዲያፈራ ገርዞ ያጠራዋል።
መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ አእምሮአችሁን በማደስ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉት።
በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ክፉ አካሄድ ትከተሉ ነበር፤ እንዲሁም በአየር ላይ ያሉትን የመናፍስት ኀይሎች ለሚገዛው ትታዘዙ ነበር፤ እርሱ በማይታዘዙት ሰዎች ላይ የሚሠራ ርኩሱ መንፈስ ነው።
የእኛ ውጊያ ከሰዎች ጋር ሳይሆን በዚህ በጨለማ ዘመን ከሚሠሩት ገዢዎች፥ ከባለ ሥልጣኖችና ከዚህ ዓለም ኀይሎችና ይህም ማለት በሰማይ ካሉት ከርኩሳን መናፍስት ሠራዊት ጋር ነው።
የዚህ ዓለም ሀብታሞች እንዳይታበዩ ወይም ተስፋቸውን አስተማማኝ ባልሆነ ሀብት ላይ እንዳያደርጉ እዘዛቸው፤ እንዲሁም ተስፋቸው እኛን ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን እዘዛቸው።
እነዚህ ሰዎች ያለ ኀፍረት በመዳራት በአንድነት ግብዣችሁ ላይ ሲገኙ እንቅፋት ይሆኑባችኋል፤ እነርሱ የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ነው፤ በነፋስ እንደሚገፋ፥ ዝናብ እንደሌለው ደመና ናቸው። በፍሬ ወራት እንኳ ፍሬ እንደማይገኝበት፥ ከስሩ እንደ ተነቀለና ሁለት ጊዜ እንደ ሞተ ዛፍ ናቸው።